"ልዩነታችንን ተቀብለን ሀገራችንን ማፅናት አለብን "- የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

119

ጂግጂጋ ፤ ግንቦት 01/2014(ኢዜአ) "ልዩነታችንን ተቀብለን ሀገራችንን ማፅናት አለብን " ሲሉ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

"ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች"  በሚል መልዕክት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው ፓናል ውይይት ዛሬ በጂግጂጋ ከተማ ተጀምሯል፤ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይም ተከፍቷል።

ተመሳሳይ የፓናል ውይይት ከሚካሄድባቸው 11 ከተሞች መካከል አንዱ የሆነው ጂግጂጋውን መድረክ በይፋ ያስጀመሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው።  

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት  አፈ ጉባኤው እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዝቡ በሀገራዊ ጉዳዮች የሚያወያዮ መድረኮች በዋና ዋና ከተሞች ተዘጋጅተዋል።

"ኢትዮጵያ በማሸነፍ እንደምትቀጥል ለማሳየት የሚያስችሉና የህዝቡን አብሮ የመምከር ባህሉን የሚያጎለብቱ ህዝባዊ ውይይት ይደረጋል" ብለዋል።

"ልዩነታችንን ተቀብለን ሀገራችን ማፅናት አለብን " ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ረጂም ታሪክ ያለን ሀገርና ህዝብ መሆናችን ለአለም ለማሳየት ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚሉ አካላት በእነዚህ መድረኮች ተገኝተው ሀገራችንን የሚጠቅሙ ሀሳቦች እንዲያካፍሉ ጥሪ ቀርቧል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀው መድረክ  ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ታዳሚዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ በምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

መድረኩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር  ቤት አባላት፣  የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና አርቲስቶች እንዲሁም ጋራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፣ ኦጋዞች፣ ሱልጣኖችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።  

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት"ስለኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀውና እስከ መጪው ሐሙስ የሚቆይ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

አውደ ርዕዩ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተመዘገቡ ድሎችና ያለፉ ውጣ ውረዶችን እንደሚያሳይ ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም