በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የተከሰተውን የአተት በሽታ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው

118
ሁመራ ጳጉሜ 2/2010 በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/ በሽታ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በዞኑ አስተዳደር  የማህበራዊ ልማት አስተባባሪ አቶ ተሻለ አስመላሽ ለኢዜአ እንደገለጹት በሽታውን ለመከላከል በዞኑ  አራት ጊዜያዊ የህክምና ማእከላት ተከፍተዋል፡፡ ጊዜያዊ የህክምና ማእከላቱ በዞኑ ጸገዴ ወረዳ ሐድነት ቀበሌ፣ በወልቃት ወረዳ ቆራሪትና መጉእ ቀበሌና በቃፍታ ሁመራ ደግሞ ማይ ካድራ በተባሉ ቦታዎች ነው የተከፈቱት፡፡ ማእከላቱ እስከ አሁን በበሽታው የተያዙ 109 ህሙማን ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በሰቲት ሑሞራ ካሕሳይ አበራ  ሆስፒታል ህክምና ተደርጎላቸው በመልካም ሁኔታ ላይ ከሚገኙት ህሙማን መካከል ወጣት በሪሁ ግዛው  አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው የበሽታው ምልክት እንደታየበት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄዱ አሁን በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በቃፍታ ሑሞራ  በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩጽ  አቶ ይብይን በርሀ  በበኩላቸው የበሽታውን ሁኔታ አስመልክቶ ለሰራተኞቻቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መቀሌ ከተማና አካባቢው እንዲሁም በማእከላዊ ዞን አሕፈሮም ወረዳ የአተት በሽታ መከሰቱን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀጎስ ገደፋይ ናቸው፡፡ በሽታውን ለመከላከል ከሀይማኖት መሪዎች በተጨማሪ፣ የውሀ ሀብት ቢሮ፣ የአካባቢ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመቀሌ ያለውን ችግር ለመፍታትና ሌሎች የክልሉ ከተሞች አርአያ የሆነ የጽዳት ስራዎች ለማከናወን  በቢሮ ሀላፊው የሚመራው ግብረሀይል ትናንት ተቋቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም