በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ እንገኛለን

184

ሚያዚያ 30/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት ገለጹ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በ27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ተቋም እንዳይኖር ከሰራባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሰራዊቱ አደረጃጀት አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የሰራዊቱ ተቋማዊ አደረጃት ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት ብቻ እንዲሰራ ተደርጎ መዋቀሩ የሚታወስ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ ወዲህ ውጤታማ ሪፎርም ከተከናወናባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሰራዊት ዋነኛው ነው፡፡

በዚህም የመከላከያ ሰራዊትን ኢትዮጵያን በሚመስልና በሚመጥን አግባብ ማደራጀት ተችሏል፡፡

በዚህም የመከላከያ ሰራዊቱ "ኢትዮጵያን እኔ ካልመራኋት ትፍረስ" በሚል እሳቤ አገር ለማፍረስ የተነሳውን የህወሃት ሽብር ቡድን ጥቃት በመመከት ኢትዮጵያን ከብተና ማዳን ችሏል።

ኢዜአ በምዕራብ ግንባር ተገኝቶ ያነጋገራቸው የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት እንዳሉት፤ ሰራዊቱ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን የክህደት ጥቃት በመመከት የተሻለ አገራዊ ቁመና ይዞ ተደራጅቷል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በህልውና ዘመቻው የህወሓትን የሽብር ቡድን ሽንፈት አከናንበው ከተመለሱ በኋላ በነበራቸው ጊዜ በቂ ስልጠና ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ከጠላት ለመመከት የወትሮው ዝግጁነት እንደማይለያቸው በመግለጽ።

ለእናት አገራችን ሉዓላዊነት መከበርና ለህዝቦቿ ሰላም መረጋገጥ እስከህይወት መስዋዕትነት ስንከፍል ቆይተናል፤ የቀድሞ አይበገሬነትና ዝግጁነት ዛሬም አብሮን አለ ብለዋል።

ወታደር ለእናት አገሩ ህልውና የመጨረሻ ምሽግ ሆኖ የሚያገለግል የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ገልጸው፤ የሚሰጣቸውን አገራዊ ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነን ብለዋል።

የትኛውንም ጉዳይ ማከናወን የሚቻለው አገር ሲኖር ነው የሚሉት የሰራዊቱ አባላት፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ወታደር ሆኖ አገሩን ማገልገል አለበት ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም እንደትላንቱ ከጎናችን በመሆኑ የኢትዮጵያ ህልውና የመጨረሻ ምሽግ ሆነን ለማገልገል ቀን ከሌት እየሰራን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሰላም የምትሆነው በወታደር ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ተባብሮ ለአገሩ ዘብ መቆም ሲችል መሆኑን ያሳለፍነው ታሪካችን ምስክር ነው  ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም