የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለፍቅርና ለአብሮነት እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

136

ሚያዚያ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለፍቅርና ለአብሮነት እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ  'አዲስ አበባ የሰላምና የአብሮነት ከተማ' በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሄዷል፡፡

በመርሃ ግብሩም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የመዲናዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከንቲባዋ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለፍቅርና ለአብሮነት እንጂ ለጥላቻ ጊዜ የለንም ነው ያሉት፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ያላቸውን አብሮነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ትልቅ  አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳዊት ትርፉ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር ተያይዞ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ይህም ለዜጎች ጤና ስጋት ከመሆን ባሻገር ኢትዮጵያ ለመድሃኒት ግዢ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታወጣ እያደረጋት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለማስ ስፖርት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው፤ የህብረተሰቡ ተሳትፎም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት በከተማ ደረጃ የተደረገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በየሳምንቱ በተመረጡ ቦታዎች ላይ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በጤናና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎችም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ በስነ-ምግባር የተናጸ አገር ወዳድ ትውልድ ለመገንባት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የስፖርታዊ እንቅስቃሴ መርሃ-ግብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም