የ” ሸዋል ኢድ” በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር

178

ሐረር ፤ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የ” ሸዋል ኢድ ” በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጋቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ አስታወቁ።

ኮሚሽነሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የ“ሸዋል ኢድ”ን በዓል ለማክበር በሀገር ውስጥና ውጭ የሚኖሩ ሃረሪዎች፣ ዳያስፖራዎች፣ቱሪስቶች እና ሌሎች እንግዶች እንደሚመጡ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓሉም ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላምና በድምቀት  እንዲከበር ፖሊስ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የጸጥታ ሃይል ጋር ግብረ ሃይል አቋቁሞና እቅድ አውጥቶ   ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በዓሉ በሚከበርበትና በዋና ዋና ስፍራዎች ላይ ግብረ ሃይሉ  ላይ ከትናንት ጀምሮ አስፈላጊው ጥበቃ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡም ከጸጥታ አካላት ጋር  ተቀናጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ  እንደሚገኝ አመላክተዋል ።

በክልሉ በዓሉ በሚከበርበት  ስፍራ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም መንገዶች ዝግ እንደሚሆኑ ኮሚሽነር ነስሪ ተናግረዋል።

በተለይ በበዓሉ የሚታደሙ እንግዶች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ክልሉ እንደሚመጡ የሚጠበቅ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤  ህብረተሰቡ በየትኛውም ስፍራ አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው  በነጻ የስልክ መስመር በ8848 ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ይፋ አድርገዋል።

ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር እያከናወነ የሚገኘውን ሰላም የማስከበር ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነር ነስሪ ጥሪ አቅርበዋል።