ኢትዮ-ቴሌኮም ከሰባት ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈረመ

275

ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በአገር አቀፍ ደረጃ ከሰባት አጋር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር የቴሌኮም ምርትና አገልግሎቶችን ለማቅረብና ለማከፋፈል የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በ633 የራሱ የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም በ134 የወኪል የሽያጭ ማእከላት አማካኝነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም ምርትና አገልግሎቶቹን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንዲያስችለው የተቋሙን ምርትና አገልግሎቶቹን በብቸኛ አጋርነት ዋና አከፋፋይ በመሆን ከሚሰሩ ሰባት ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ስምምነት አድርጓል።

ኢትዮ- ቴሌኮም ስምምነቱን የተፈራረመው ከህዳሴ ቴሌኮም አክስዮን ማህበር፣ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ናሬድ ጄኔራል ትሬዲንግ፣ ሃይላይት ስቴሽነሪና ማኑፋክቸሪንግ ትሬዲንግ፣ ስማርት ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ አላሚ ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ እና ከቴሌፖርት ቴክኖሎጂስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ነው።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ተቋሙ የጀመራቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች በአጋሮቹ አማካኝነት ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ለማድረስ በማስቻል ረገድ ትልቅ ሚና አለው።

ተቋሙ ከ7ቱ አጋር ድርጅቶችና ተቋማት ባሻገር ከነባር 48 አካፋፋዮች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱን ያደረጉት ተቋማት እንደ ቴሌብር አገልግሎት፣ የሞባይል ሲምካርድ እና አየር ሰዓት እንዲሁም የምትክ ሲምካርድ አገልግሎቶችን ከአጋሮች ጋር በጋራ በመስራት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ስራ የሚሰሩ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ተቋሙ አጠቃላይ የአከፋፋዮቹን ቁጥር ወደ 68 ያደረሰ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይህም ከ1 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስችለውም ጠቁመዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 64 ሚሊዮን የሚሆን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም