ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት አጀንዳ የሚፈጥሩ ጽንፈኞችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ ሚናውን እንዲወጣ ተጠየቀ

120

ባህር ዳር ፤ሚያዚያ 28/2014 ሃይማኖትንና ብሄርን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት አጀንዳ የሚፈጥሩ ጽንፈኛና አክራሪ ግለሰቦችን ለማጋለጥ ህብረተሰቡ ሚናውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

በንፋስ መውጫ ከተማ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመቋቋም የሚያግዝ የገቢ ማስባሰቢያ ቴሌቶን ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት   ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሃይማኖቶች ለዘመናት ያዳበሩት መቻቻልና መከባበር ለዓለም ምሳሌ ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን አንድነትና ለውጥ የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ  ሃይሎች በሚሰጡት አጀንዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች መከሰታቸውን አውስተዋል።

በተለይም አሁን ላይ አሸባሪው ህወሃት ከሌሎች መሰሎቹ ጋር በማበር  ተለያይቶ የማያውቀውን ህዝብ በማለያየት የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን አቶ አማረ አስረድተዋል።

በሃይማኖትና ብሄር ሽፋን  ህዝቡን እርስ በእርስ ሊያጋጩ የሚጥሩ ጽንፈኛና አክራሪ ግለሰቦችን ማህበረሰቡ ለማጋለጥ ሚናውን በመወጣት  ለዘመናት ይዞት የመጣውን የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህሉን እንዲያጠናከር ጠይቀዋል።

ምክትል አፈ -ጉባኤው ፤ አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት መመከት እንደተቻለው ሁሉ አሁንም ተላላኪ ጽንፈኞችንና አክራሪዎችን በማጋለጥ የቀደመ ክብራችንን ማስጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስከፊነት በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል  የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህውሃት በጦርነት የጀመረው ሀገር የማፍረስ ሴራ ቢከሽፍም፤ በአክራሪዎችና ጽንፈኞች በኩል ሴራውን ለማስፈጸም ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በቅርቡ በአሸባሪው ህወሃት  እኩይ ሴራ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩ የክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለማጋጨት ያደረገው ሙከራ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የተጠነሰሰውን ሴራ በማክሸፍ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

“አክራሪነትና ጽንፈኝነት ሃይማኖትና ብሄር የለውም” ያሉት አቶ መልካሙ፤ ሁለቱም ወንጀል በመሆናቸው የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በጋራ እንዲከላከሏቸው  አስገንዝበዋል።

በንፋስ መውጫ ከተማ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እንዲያግዝ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን የመጀመሪያው ቀን 25 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።