የምስራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎች እያጋጠማቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ

89

ሐረር፤ ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች በየደረጃው ባለው የአስተዳደር እርከን እያጋጠማቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ።

ከዞኑ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር የተወጣጡ  ነዋሪዎች  በልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ በባቢሌ ከተማ ከአመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ነዋሪዎቹ በፍትህ ተቋማት በተለይም በአቃቢ ህግና ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ሰዎችን ያለማስረጃ ማሰር ብሎም  በህግ ጥላ ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች   ከህግ አግባብ ውጪ  ለፍርድ ሳይቀርቡ በእስር ቤት   ለወራት እንደሚቆዩ አንስተዋል፡፡

የመንገድ  ፣የኤሌክትሪከ መብራት፣ የመጠጥ ውሃና  የጤና አገልግሎት እንዲሁም  የመድሃኒት አቅርቦት ችግሮች እንዳሉባቸውም አመልክተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች  አቶ ሀመድ አብዱረህማን በሰጡት አስተያየት፤ በሚኖሩበት ጃርሶ ወረዳ  ከአቃቢ ህጎችና ፖሊስ አባላት ጋር በተያያዘ ከስነምግባር ያፈነገጡ  ተግባራት እንደሚፈፀሙ በመግለጽ  አስተዳደሩ  ስርዓት እንዲያሲያዛላቸው ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ  ተሳታፊ አቶ ኢብራሂም አብዱላሂ፤  በጉርሱም ወረዳ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ  ወረዳዋ ልታድግ እንዳልቻለች ገልጸው፤ ጉርሱምን ከባቢሌ የሚያገናኝ መንገድ እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል ፡፡

አያይዘውም በወረዳው  የመብራትና የመጠጥ ውሃ ችግር መኖሩን  ጠቅሰው፤ የተገነባው ሆስፒታልም  የባለሙያ  እጥረትና የመድሃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ለጤና መድን  ካርድ አውጥተው ለመታከም ወደጤና ጣቢያ ቢሄዱም  አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ  መሃመድ ሃሰን ናቸው ፡፡

" ጥሬ ገንዘብ ከፍሎ ለሚታከሙ ሰዎች ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፤ ለጤና መድን ከፍለን በተሰጠን ካርድ  ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንድንችለ መንግስት በትኩረት መስራት አለበት" ብለዋል፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ በሰጡት ምላሽ ፤ ህብረተሰቡ ያነሳቸው  ችግሮች ቀድሞ መረጃው የደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሮቹን ለመፍታት የመለየት ስራ መጀመሩንና ቀጥሎም የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀዋል፡፡

የማህበረሰቡ  የመሰረተ ልማት ችግርም በተግባር ሰርቶ ምላሽ ለመሰጠት ይሰራል ብለዋል ፡፡

የማህበረሰቡን  ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተያዘው እቅድ መሰረት  ሀላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት ከስልጣን ማውረድ እስከ ስራ ማሰናበት የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት  ገልጸዋል፡፡

ያለ አግባብ የወጣ  ከ580 ሺህ ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ  ተመላሽ  ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በዞኑ በዓመቱ ከ 71ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን፤  ከ144 ሚሊየን ብር  በላይ ብድር መሰጠቱንና ከ42 ሚሊየን ብር በላይ  የብድር ገንዘብ ተመላሽ መደረጉንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም