የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ የማድረስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል

124

ሚያዝያ 28/2014 (ኢዜአ) የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ የማድረስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያቻቸው የተግባቦት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የአቅም ማጎልበት ስራ ማከናወን እንደሚኖርባቸውም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት(ኢባትሎድ) ጋር በመተባበር ከሚያዚያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ስልጠናው ዴቨሎፕመንት ኮምዩኒኬሽን’፣ መልዕክት ቀረጻ፣የሐተታ ዜና አጻጻፍና ና ዜና ትንታኔ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።

የኢዜአ የስልጠና፣ምክርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ናስር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎች ለሕብረተሰቡ ማድረስ ዋነኛ ተግባራቸው አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት የመረጃ ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎቹ በመገንዘብ ለፍጥነትና ለተደራሽነት እንዲተጉ  መክረዋል።

እንደ ኢባትሎድ ያሉ ስትቴጂካዊ ተቋማት የሚሰሩትን ስራ በተመለከተ የመረጃ ተደራሽነታቸውን በማስፋት የተገልጋዮቻቸውን እርካታ ማረጋገጥ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ስልጠናውም የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃዎችን በምን ዓይነት መልኩ ወደ ሕብረተሰቡ ማድረስ አለባቸው? በሚለው ጉዳይ ግንዛቤ የመፍጠር አላማ ያለው እንደሆነም ነው አቶ አብዱራህማን ያስረዱት።

ኢዜአ ከኢባትሎድ ጋር በስልጠናና ሌሎች መስኮች ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው ድርጅቱ ከኢዜአ ጋር ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ስልጠናው ሁለቱ ተቋማት ያላቸው  የትብብር አካል ማሳያ መሆኑንና ግንኙነቱ ይበልጥ መጠናከር እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

ኢባትሎድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለው ፋይዳ አኳያ ድርጅቱ የሚያከናውናቸውን ስራዎች በተለያዩ የተግባቦት ዘዴዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባውና ለዚህም ስልጠናው የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ስልጠናውን መነሻ በማድረግ መረጃዎችን በፍጥነት ማህበረሰቡ ጋር ተደራሽ የማድረግና የማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መልኩ እንዲወጡ አቶ ደምሰው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ጨምሮ ለ15 የፌደራል ተቋማት የመገናኛ ብዙሃንና ተግባቦት የተመለከቱ ስልጠናዎችን ለሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1115/2011 ተቋሙ ገቢ የሚያስገኙለትን እንደ የሕትመት፣የጥናትና ምርምር፣የስልጠናና የማማከር፣ የፕሮዳክሽን፣ ኩነቶችና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችንና ዘጋቢ ፊልሞች ያሉ አገልግሎቶችን ለሌሎች ተቋማት መስጠት እንደሚችል ያስቀምጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም