ኮሚሽኑ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ድረ-ገጽ ይፋ አደረገ

109

ሚያዚያ 28/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን በአገሪቱ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የተመለከቱና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ድረ-ገጽና የዲጅታል ላይብረሪ ይፋ አደረገ።

የኮሚሽኑ የዲጂታል መረጃና የእውቀት ማዕከል ድረ-ገጽ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች  የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።  

የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ መረጃዎችን በቀላሉ ለሚመለከተው ለማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂን አበልጽጓል።

ተቋሙ በአገሪቱ አደጋ ከመድረሱ በፊት የቀድመ ማስጠንቀቅ ሥራ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ይሰራል።

እነዚህን ተግባራት ለማከናወንና በአግባቡ የተደራጀና በቀላሉ ለኅብረተሰቡ መረጃ የሚያደርስበት ቴክኖሎጂ ያስፈልጋዋል።

በዚህም ሳቢያ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የዋጀ ድረ-ገጽ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል ብለዋል።

ለኅብረተሰቡም የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥራዎችን በቀላሉ በማግኘት ራሳቸውን ከተፈጥሮ አደጋ በፍጥነት እንዲከላከሉም ይረዳል ነው ያሉት።

በተለያዩ አጋር አካላት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲሰራ የነበረው ድረ-ገጽ የተቋሙን አገልግሎት ለማሳለጥና ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

በተለይም በጥናት የተለዩና የዕለት ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በመለየትና መረጃን ከአንድ ቋት በማግኘት  የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሎች የተደራጀ መረጃን ከዲጂታል ላይብረሪና ከድረ-ገጹ በመውሰድ ለተጎጂዎች ፈጣን ድጋፍ ለማድረግ ያግዛቸዋል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ edrmc.gov.et በተሰኘ የድረ-ገጽ አድራሻ በመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም