በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የጎብኝዎች ቁጥር በእጥፍ ጨመረ

57
ጎንደር ግንቦት 10/2010 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ባለፉት 9 ወራት የጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች በእጥፍ መጨመሩን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አስጎብኚዎችና የኢኮ-ቱሪዝም ማህበራት በሚሰጡት አገልግሎት የክልሉ መንግስት አዲስ የታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት 9 ወራት 15ሺ 176 የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን ጎብኝተዋል፡፡ የውጪ ሀገር ቱሪስቶቹ ቁጥር ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ7ሺ 500 ማደጉን የገለጹት ሃላፊው ''ለቱሪስቶች ቁጥር ማደግም ባለፈው አመት በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተወግዶ ሰላም በመስፈኑ ነው'' ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የፓርኩ መዳረሻ በሆነው ደባርቅ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና የቱሪስት መዝናኛና ማረፊያ ሎጅዎች  ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በባለሀብቶች መገንባታቸው ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከውጪ ሀገር ቱሪስቶቹ በተጨማሪም 1ሺ 94 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ ቱሪሰቶችም በ9 ወራቱ ፓርኩን ጎብኝተዋል ብለዋል ፡፡ በ9 ወራቱ የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑ 5 ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለቱሪስቶች ምግብ በማብሰል ፣ ጓዝ በመጫን ፣ በቅሎ በማከራየትና  በማስጎብኘት ጭምር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ፓርኩ ከቱሪስቶች የመግቢያ ትኬት፣ ከመኪና ኪራይ፣ ከቦታና ከፊልም ቀረጻ ስራ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡና መንግስት ያገኙት ገቢም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል ያሉት ኃላፊው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር የህብረተሰቡና የመንግስት ገቢ በአምስት ሚሊዮን ብር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡን ከቱሪዝም ገቢው ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረትም በዚህ አመት መጋቢት ወር ላይ የክልሉ መንግስት የቱሪስት አገልግሎት ለሚሰጡ አስጎብኚዎችና የኢኮ-ቱሪዝም ማህበራት የታሪፍ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ወስኗል፡፡ በውሳኔው መሰረት ከዚህ ቀደም ለቱሪስቶች ጓዝ በመጫንና በቅሎ በማከራየት ለበቅሎ ጫኝ ማህበር አባላት በቀን ይከፈል የነበረው 120 ብር አበል  ወደ 400 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ በቱሪስት አስጎብኝነት ስራ በፓርኩ አካባቢ የተደራጁ ወጣቶችም ከዚህ ቀደም ከ1 እስከ 5 የሚደርሱ ቱሪስቶችን የሚያስጎበኙበት የቀን አበል ከ300 ብር ወደ 500 ብር ማደጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በደባርቅ ከተማ የበቅሎ አከራዮችና ጓዝ ጫኚዎች ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ ማረው ተረፈ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማህበሩ አባላት ለቱሪስቶች ጓዝ በመጫንና በቅሎ በማከራየት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ማህበሩ ያገኘው ገቢ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት ሚሊዮን ብር ብልጫ መኖሩን አመልክተዋል፡፡ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በውስጡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ ነው፡፡ በዚህ ዓመት 28 ሺህ ቱሪስቶች የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እንዲጎበኙ በእቅድ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም