ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሙት የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ሥምምነት የቀጣናውን ኃይል ትስስር ያጠናክራል

152

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሙት የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ሥምምነት የቀጣናውን የኃይል ትስስር እንደሚያጠናክር የሁለቱ አገራት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርማለች።

ሥምምነቱንም የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ እና የደቡብ ሱዳን የውኃና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ዛሬ ማምሻውን ፈርመውታል።

የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ሲሆን በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ነው ተብሏል።

በሥምምነቱም የኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ-ልማት ግንባታዎችን በሁለቱ አገራት በኩል በማከናወን ከሦስት ዓመት በኋላ ኃይሉን ወደ አገሪቱ ተደራሽ በማድረግ ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቃል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹም ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ከጋምቤላ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳኗ መልካን ከተማ 357 ኪሎ ሜትር የ250 ኪሎ-ቮልት መስመር ዝርጋታን ያካተተ ነው።

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከ400 እስከ 500 ኪሎ-ቮልት ተሸካሚ መስመሮችን ኤሳ ቴፒ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የሚዘረጋ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው ተብሏል።

የኃይል ማስተላለፊያ ሥፍራዎች የአዋጭነት ጥናት በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ የመሰረተ-ልማት ግንባታው ሥራ ይጀመራል ተብሏል።

የኃይል መሰረተ-ልማት ዝርጋታውም በሁለቱ አገሮችም ሆነ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት እንደሚሸፈንና ጥምር ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው የተገለጸው።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ለልማት ሳይሆን ለንትርክ እንደዳረጓት ገልጸው፤ ድንበር ተሻጋሪ ኃብቶችን በሥምምነት ተጋርቶ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥና በጨለማ ውስጥ ያሉ ዜጎቿን ወደ ብርሃን ከማጎናጸፍ ባለፈ ለጎረቤት አገራት የሚተርፍ ኃይል ለማመንጨት እየሰራች ስለመሆኗ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ለአብነት አንስተዋል።

በዕለቱ የተደረገው ሥምምነቱም አንድም የሁለቱን አገራት ዜጎች ሕይወት ለመለወጥ ብሎም እንደ አፍሪካ በቀጣናው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሱዳንን ጨምሮ ለጎረቤት አገራት ኃይል አመንጭቶ ማቅረቧ ከሁለትዮሽ የማኅበረ-ኢኮኖሚ ዕድገትና ለአገራቱ ጠንካራ ትስስር ወሳኝ በመሆኑ መግባቢያ ሥምምነቱም የዚህ አካል ነው ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን የውኃና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ በበኩላቸው፤ የኃይል ሽያጭ መግባቢያ ሥምምነቱ የቀጣናዊ ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ሥምምነቱ ደቡብ ሱዳን እንደ ሱዳንና ጅቡቲ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኃይል ትስስር ያጎለብታል ብለዋል።

ሚኒስትሮቹ ሥምምነቱ ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ አገራቱ ለኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ ገቢራዊነትና ለመሰረተ-ልማት ዝርጋታው ቁርጠኛ መሆናቸውን  አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ለሱዳንና ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ እያገኘች ሲሆን ከኬንያ ጋርም የሽያጭ ሥምምነቱን ፈፅማ በራሷ የሚጠበቀውን የኃይል መሰረተ-ልማት ግንባታዋን ፈፅማለች።