በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀው ውጤት እንዲመዘገብ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተመለከተ

139

አሶሳ፣ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀው ውጤት እንዲመዘገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተመላከተ፡፡

በክልሉ በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 513ና ከዛ በላይ የሆነ ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ 18 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

በሽልማት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ እንዳሉት፤ በክልሉ የሰላምና ጸጥታ ችግር እያለ ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት የሚበረታታ ቢሆንም የትምህርት ዘርፍ ካለው የሰው ሃይል፣ በጀትና ሌሎች ግብዓቶች አንጻር ውጤቱ አጥጋቢ አይደለም።

“መምህራንን ለመመዘን የሚሰጠው የብቃት መመዘኛ ፈተና ውጤት የሚያሳየው ክፍተት መኖሩን ነው” ያሉት አማካሪው፤  የመምህራኑን ብቃት ለማሳደግ በክልሉ የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ኮሌጆች በሚገባ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የዘርፉን ችግር ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የተማሪዎችን ውጤት በሚጠበቀው ደረጃ ለማሳደግ ከአንድ ተቋም ባሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ  የክልሉ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ካሚል ሃሚድ ናቸው።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር የትምህርት ጥራትን ማሳደግ ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ መስራት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

አመራሩ ከተማሪዎች፣ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ችግሮችን መፍታት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጃፈር ሃሩን በበኩላቸው ትምህርትን ተደራሽ ማድረግና ጥራትን ማስጠበቅ የትምህርት ቢሮ ሃላፊነት ብቻ ተደርጎ መታየቱ  ዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ማድረጉን  ተናግረው ሁሉም የሚጠበቅበትን መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።