የኃይማኖት ተቋማትን ኢላማ በማድረግ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን ሴራ ህዝቡ ሊያከሽፈው ይገባል

96

ሚዛን፤ ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኃይማኖት ተቋማትን ኢላማ በማድረግ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ ሳይዘናጋ ሊያከሽፈው እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስገነዘበ።

ጉባዔው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ በማስመልከት በሚዛን አማን ከተማ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የጉባዔው ተወካዮች አካባቢያቸውንና ቤተ እምነቶችን ከተላላኪዎች እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

የጉባዔው ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን አረጋ ጠመረ በመግለጫቸው እንዳመላከቱት የኢትዮጵያን አንድነትና ህብረት ሊፈታተን የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቱን ለማፍረስ ያቀዷቸው ውጥኖች ሁሉ አልሳካ ሲላቸው በኃይማኖት ሽፋን ሀገር ለማተራመስ መከሰታቸውን አውስተዋል።

"ያለንን ጠንካራ የሃይማኖት እሴት ተጠቅመን ሴራቸውን እናከሽፋለን እንጂ፤ ባጠመዱት ወጥመድ ገብተን ኢትዮጵያን የምናፈርስ አይደለንም" ሲሉም ተናግረዋል።

በእስልምና እና በክርስቲያን አማኞች መካከል ግጭትና ጥፋት ለማቀጣጠል የሚደረግ እንቅስቃሴ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው  ሊቀ ትጉሃን አረጋ ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ ሳይዘናጋ እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

የጉባኤው  ምክትል ሰብሳቢ ሐጂ አባ ነጋ አብዱልከሪም በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ተጋግዘው ቤተ እምነቶችን የሚገነቡ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸው፤ "ይህንን ሀቅና ህብረታችንን በማንም አናስነጥቅም" ሲሉም ተናግረዋል።

"እሳትን እሳት አያበርደውምና ነገሮችን ሰከን ብሎ መመልከትና ለመፍትሄው በጋራ መምክርና መፍትሄ ላይ መድረስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የጉባዔው ጸሐፊ ቆሞስ አባ ጴጥሮስ አበበ በበኩላቸው የሰውን አብሮነት የሚያናጋ የሃይማኖት አስተምህሮ በሁሉም ቤተ እምነቶች እንደሌለ ተናግረዋል።

የጉባዔው አባልና የዞኑ ወንጌላውያን አማኞች ቤቴል ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ቄስ እንድሪያስ እሴይ የሃይማኖት ግብ መንግሥተ ሰማያት ወይም ጀነት መውረስ መሆኑን ይገልጸዋል።

አሁን በእምነት ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ ያሉት ተግባራት ግን ይህንን የሚቃረኑ በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማትን አይወክሉም ብለዋል።

የዚህ መሰሉ ድርጊትና ጥፋት እንዳይስፋፋና ሀገሪቱን ከጥፋት ሃይሎች ለመታደግ የሁሉም ሃይማኖቶች  አባቶች አርዓያ ሆነን ለሰላምና አንድነት መሥራት አለብን ሲሉ በአፅኖት ተናግረዋል።

የጉባዔው ተወካዮች አካባቢያቸውንና ቤተ እምነቶችን ከተላላኪዎች በመጠበቅ ሰላምን ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም