አዲስ አበባ በነገው ዕለት ከተማ አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ታከናውናለች

89
አዲስ አበባ ጳግሜ 2/2010 አዲስ አበባ በነገው ዕለት ከተማ አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ታከናውናለች። ከተማ አስተዳደሩ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ “በአዲስ  ዓመት ፅዱና ውብ አዲስ አበባ” የተሰኘ የፅዳት ዘመቻ እንደሚከናወን ይፋ አድርገዋል። የከተማው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጅት ደበላ እንደገለፁት በነገው ዕለት በከተማው አትክልት ተራና ካራን ጨምሮ በቆሻሻ የሚታወቁ  96 የከተማው ሥፍራዎችን ማዕከል ያደረገ የፅዳት ዘመቻ ይካሄዳል። በአትክልት ተራ በሚካሄደው የፅዳት ዘመቻ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የከተማው ባለስልጣናትና ሰራተኞች ይሳተፉበታል ብለዋል። የአስሩም ከፍለ ከተማ አመራሮች በየአካባቢያቸው በሚካሄደው ፅዳት እንደሚሳተፉ የተናገሩት ወይዘሮ ቆንጅት የፀዱ ሥፍራዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ርክክብም ይካሄዳል ብለዋል። የከተማው የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጄንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ለማ በበኩላቸው ሁሉም የከተማው ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ አካባቢውን በማፅዳት አዲሱን ዓመት አንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል። "አከባቢን ማፅዳት ባህላችን ሊሆን ይገባል" ያሉት አቶ እሸቱ ኤጄንሲው በአዲሱ በጀት ዓመት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሥፋት ለማከናወን መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ያለውን የግል የፅዳት ማህበራት ተሳትፎ ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን የ50 የፅዳት ተሽከርካሪዎች ግዢም እየተከናወነ መሆኑን አቶ እሸቱ ገልፀዋል። በሌላ በኩል የቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችም በፅዳት ዘመቻው እንደሚሳተፉ የክለቡ የደጋፊ ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ክፍሌ ወልዴ ተናግረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የክለቡ ደጋፊዎች በፅዳት ዘመቻው እንደሚሳተፉ የተናገሩት አቶ ክፍሌ ከጅግጂጋ ከተማ ለተፈናቀሉ ዜጎች አልባሳትን የማሰባሰብ ሥራም እናከናውናለን ብለዋል። በህዳር 2010 በጀት ዓመት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የተጀመረው “እኔ  አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ?” የተሰኘው ወርሃዊ የፅዳት ዘመቻ ሞዴል የሆኑ ፅዱ መንደሮችን ለመፍጠር ማስቻሉን ወይዘሮ ቆንጅት ተናግረዋል። በተለይ በኮንደሚኒየሞችና ሪል ስቴቶች አካባቢ ፅዱ መንደሮች ተፈጥረዋል ያሉት ወይዘሮ ቆንጅት የተጀመረው ወርሃዊ የፅዳት ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም