በጽኑ አለት ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ አንድነት በጽንፈኛ ሃይሎች እኩይ ተግባር አይፈርስም - የሃይማኖት አባቶች

137

አርባ ምንጭ ሚያዝያ 26/2014(ኢዜአ) በጽኑ አለት ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ አንድነት ጽንፈኛ ሃይሎች በጠነሰሱት ሴራና እኩይ ተግባር የማይፈርስ መሆኑን በደቡብ ክልል የጋሞ ዞን የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ፡፡

በሃይማኖት ሽፋን በጎንደርና ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የተፈጸሙ እኩይ ተግባራት ሃይማኖቶችን የማይወክሉና ሊወገዙ የሚገባ መሆኑን የሀይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን እስልምና ጉዳይ ዋና ፀሐፊ ሼኽ መሃመድ ሁሴን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት በጽኑ አለት ላይ የተገነባ በመሆኑ ለብዙ ሺህ ዓመታት በመከባበርና በመቻቻል አብሮ ሲኖር መቆየቱን አውስተዋል፡፡

የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ተከታዮችም በመከባበር፣ በአንድነትና በፍቅር የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች  መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በጎንደርና ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ጽንፈኞች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የፈጸሙት እኩይ ተግባር የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ የተቃጣ መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱ የትኛውንም ሃይማኖት የማይወክልና ሊወገዝ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጽንፈኞች ሴራ ሃይማኖቴ ተነካብን በማለት በግብታዊነት ሌላ ጥፋት ውስጥ እንዳይገባ ህዝበ ምእመኑ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

"በተለይ በአሁኑ ጊዜ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚቃጡ እንቅስቃሴዎች መታወክ አይገባም" ያሉት ሼኽ መሃመድ መንግስት በድርጊቱ የተሰማሩ አካላትን በመከታተል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

"ኢትዮጵያዊያን ከአንድነት ውጭ የሚያዋጣን አንዳች አማራጭ የለም" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋሞና ጎፋ ሀገረ-ስብከት ዋና ፀሐፊና የአርባ ምንጭ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ መጋቢ ሰናያት ያዕቆብ ደስታ ናቸው፡፡

"እኛ ኢትዮጵያዊያን በሚያለያዩን ጉዳዮች ተቻችለንና ተከባብረን ለዘመናት የኖርን ህዝቦች ነን" ያሉት መጋቢ ሰናያት በኢትዮጵያ  የትኛውንም ሃይማኖት የሚከተል ሰው አክራሪና ጽንፈኛ ሊሆን እንደማይገባ መክረዋል፡፡

መንግስት በጎንደርና በስልጤ አካባቢ ሴረኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ጽንፈኞችን አሳልፎ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በቀልን በበቀል ለመመለስ ማሰብ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታትና በድርጊቱም ተጎጂው ህዝቡ ራሱ በመሆኑ ሁሉም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

"ያለሰላም ሃይማኖት ሊኖር የማይችል በመሆኑ ለአባባቢያችን ሰላም ዘብ በመቆም መንግስት የሚያደርገውን ተግባር በመተባበር የበኩላችንን እንወጣለን" ስሉ አስታውቀዋል፡፡

በጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች አስተባባሪ ሻምበል መስፍን አንዳርጌ በበኩላቸው "በጎንደርና ስልጤ የተከሰተው ድርጊት አስነዋሪና አሳዛኝ ነው" ብለዋል፡፡

ድርጊቱ በሃይማኖታዊ ሽፋን የተፈጸመና ጽንፈኞች የኢትዮጵያን አንድነት በመናድ ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ያደረጉት መሆኑን  ህዝቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

"ህዝቡ የጋራ ጠላት የሆነውን አካል ሊለይ ይገባል" ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ ጋሞ ዞንም  የፀጥታ አካላት ከህዝቡና ሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ለእኩይ ተግባር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በጥንቃቄ ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥሙት ለጸጥታ አካላት መረጃ እንዲሰጥ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም