በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት ጠንሳሾች ትናንት በብሔር ሊያጋጩ ሲሞክሩ የነበሩ የአሸባሪና የጽንፈኛ ቡድኖች አባላት ናቸው – ነዋሪዎች

203

ሚያዚያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት ጠንሳሾች ትናንት በብሔር ሊያጋጩ ሲሞክሩ የነበሩ የአሸባሪና የጽንፈኛ ቡድኖች አባላት መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

መንግስት በግጭቱ እጃቸውን ያስገቡ ማናቸውንም አካላት ለህግ በማቅረብ ፍትህ እንዲያሰፍንም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

በከተማዋ ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰቡ ተወካዮች ሚያዚያ 18 ቀን በከተማዋ በተከሰተው ግጭት መንስኤና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ግጭቱ ከጎንደር ህዝብ ተቻችሎ የመኖር እሴት አኳያ መፈጠር ያልነበረበት አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች ተከባብሮና ተደጋግፎ የመኖር የቆየ ታሪክ ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ግጭቱ የአሸባሪና የጽንፈኛ ቡድኖች ሴራ እንጂ የሁለቱ ሀይማኖት አይደለም ብለዋል።

የችግሩ መንስኤ የጎንደር ሰላም ያላስደሰታቸው የውጭ ሀይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው መሆናቸውንምን ገልጸዋል።

ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት በከተማዋ ሁከት ሲፈጥሩ የነበሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ያልሆኑም ጭምር መሆናቸውን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ተሰግስገው የአሸባሪውን ህወሀት አጀንዳ የሚያስፈጽሙ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በጎንደር ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ስርአቱም ሊፈተሽ እንደሚገባው የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል።

መንግስት በግጭቱ ዙሪያ እስካሁን የደረሰበትን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ህዝቡ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚሰራጨው መረጃ እንዳይወዛገብ ማድረግና ማረጋጋት አለበት ብለዋል።

ጠንካራ የመረጃ ደህንነት ባለሙያዎችን በማሰማራት ማን ምን እየሰራ ነው የሚለውን መከታተልና መቆጣጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሀይማኖት አባቶች፣ የህዝብ ተወካዮች፣ የአስተዳደር አካላት እውነተኛ መረጃ በመስጠት ሀገርን ማረጋጋት እንዳለባቸውም ተወያዮቹ ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ፤ ከማንኛውም የእምነት ተቋም የሚመጣ አክራሪና ጽንፈኛ ሀይል ለሀገርም ለማንም አይጠቅምም ብለዋል።

በመሆኑም የሀይማኖት አባቶች ጽንፈኛና አክራሪ ሀይሎች ጸረ-አንድነቶች መሆናቸውን ተረድተው ህዝቡ በስሜት ሳይሆን በአስተውሎት እንዲጓዝ በማድረግ ራሳቸውን ጭምር ከጥፋት ማዳን አለባቸው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው በተከሰተው የፀጥታ ችግር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት በሀይማኖት፣ ሀይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የሀይማኖት አባቶች በቤተ እምነት ገብተው ስለፖለቲካ ትንታኔ መስጠት ሀላፊነታቸው አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

የሀይማኖት አባቶች የሀይማኖቱ አስተምህሮ ላይ ብቻ በማተኮር ህዝቡን ሊቀርጹና ሊያንጹ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አስተዳደራዊ በደሎች ሲደርሱ መንግሥት የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ማሳየት እንጂ ጣልቃ ለመግባት መሞከር ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና መላው ህዝብ ሀገር እንድትቀጥል ከመንግሥት ጎን በመቆም የህዝብ ሰላምና አንድነት እንቅልፍ የሚነሳቸውን ሀይሎችና ተላላኪዎቻቸውን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።