በአማራ ክልል በመጪው ክረምት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው-ቢሮው

106

ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በመጪው የክረምት ወቅት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉን የደን ሽፋን 15 ነጥብ 8 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።

የቢሮው ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በመጪው የክረምት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

እስካሁን 701 ሚሊዮን የሃገር ውስጥና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ተፈልተው መዘጋጀታቸውን  ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተመናመነ 192 ሺህ 705 ሄክታር የደን መሬት ላይ ችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ አመላክተዋል ።

እስካሁንም 158 ሺህ 819 ሄክታር መሬት ለተከላ መለየቱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወናባቸው ተፋሰሶች ላይ ተከላው እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በአንድ ቀን በሚከናወን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ከ250 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በክልሉ ዘንድሮ በሚተከሉት ችግኞች የደን ሽፋኑን 15 ነጥብ 8 በመቶ ለማድረስ  መታቀዱን አመልክተዋል።

መርሃ ግብሩን ለማሳካት ወደ ዞኖች ተወርዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በ185 ሽህ 151 ሄክታር መሬት ላይ  ለተተከሉ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች በተደረገ እንክብካቤና ጥበቃ 84 በመቶ  መጽደቃቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተካሄደ የደን ልማት እንቅስቃሴ የደን ሽፋኑ 15 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም