በአባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠየቀ

93
አርባምንጭ ግንቦት 10/2010 አባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ በሚደረገው ዘመቻ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የደቡብ ክልል አከባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ። ሐይቁን ከአረም የመከላከል ክልል አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ትናንት በአርባምንጭ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ የክልሉ አከባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡን በስፋት በማሳተፍ ከአባያ ሐይቅ እምቦጭን ለማስወገድ እየሰራ ነው። "ሐይቁ ከክልሉም አልፎ የሀገር ሀብት ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከግንቦት 15 ጀምሮ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በሚካሄደው ዘመቻ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል። አረሙን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንዲቻል ከግንቦት 15 ጀምሮ በዘመቻ የሚጀመረው ስራ ለአንድ ወር ይቆያል፡፡ በዘመቻው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ባላቸው አቅምና ጉልበት  በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቋል። የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በበኩላቸው አረሙ በሀይቁ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የዞኑ አስተዳደር ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም ከ29 ሺህ በላይ በሐይቁ ወሰን አካባቢ ላሉ ነዋሪዎች በአረሙ አወጋገድ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። በሐይቁ ዳርቻ በተከሰተው አረም ላይ ምልከታ በማድረግ 4 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ማሰወገድ መቻላቸውንም ገልጸዋል። ይህም ቀጥሎ ለሚከናወነው ስራ መልካም ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከ54 በላይ ብዝሃ ህይወት በያዘው አባያ ሐይቅ ላይ አረሙን የማስወገድ ስራ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና የምርምር ተቋማት ስራውን እንዲያግዙ ተጠይቀዋል፡፡ የፌደራል ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ካንቹላ በሰጡት አስተያየት እምቦጭ አረም በክልሉ ከአባያ ሐይቅ በተጨማሪ በኩሬዎችና ወንዞች ዳርቻም እየተስፋፋ ነው። አረሙን በጋራ ትኩረት በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ ግልገል ጊቤ ሶስትን ጨምሮ የሌሎች ሐይቆችና ወንዞች ስጋት መሆኑን ገልጸዋል። ትናንት በአርባምንጭ ከተማ በተጀመረውና ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ ባለድርሻ አካላት፣ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች በመሳተፍ በአረሙ አወጋገድ ዙሪያ እየተወያዩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም