ህዝብ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ እናከሽፋለን-የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

184

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 24/2014 (ኢዜአ) እስልምና የሚያስተምረው ጥፋትን በጥፋት ሳይሆን፤ ምዕመናንን በማስተማር በመሆኑ ህዝብ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ አልመው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ እናከሽፋለን ሲሉ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ አስታወቁ።

በባህር ዳር ከተማ 1ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በተለያየ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ ሃይማኖትን ሽፋን አደርገው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ ለማምከን ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች በደረሰው ጉዳት ሁላችንም ተጎጂዎች ነን ብለዋል ሼህ ሰይድ።

ቤተ እምነቶች ለዘመናት የዘለቀውን የመቻቻል፣ የመፈቃቀር፣ የመዋደድና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶች ማጠናከር ይገባናልም ብለዋል።

መንግሥት በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም እንደሚገባው ተናግረዋል።

ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ የፖለቲካ ጥቅመኞች በየአካባቢው የሚፈጥሩትን ግጭት ህዝበ ሙስሊሙ ከመንግሥት ጋር በመተባበር እንዲያከሽፈው የጠየቁት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዬ አለባቸው  ናቸው።

የውጭና  የውስጥ ፀረ ሰላም ሃይሎች ብሄርና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሀገር ለማተራመስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ  ክፍሎች ሰሞኑን  የተከሰቱት ግጭቶች ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን አብሮ የመኖር እሴት ለመናድ የሚፈልጉ ሃይሎች ጥንስስ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት አጥፊዎችን በመለየት ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝበ ሙስሊሙ ትብብር እንዲያደርግ ምክትል ከንቲባው ጠይቀዋል።

የከተማዋ የሙስሊም አባቶችና የወጣት አደረጃጀቶች በከተማዋ ከእምነት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይፈጠር ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም