ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

110

ሀገራችን ኢትዮጵያ ህብረ ብሄር፣ ህብረ ቋንቋ፣ ህብረ ባህልና የተለያዩ ሀይማኖቶች መገኛ ነች።

እነዚህ ሁሉ ህብረ ቀለማት የሀገራችን የኩራትና የማንነታችን መገለጫ ሁነው ለብዙ ሺህ አመታት ዘልቀዋል።

በተለያየ ጊዜ ሀገራችን ለሚገጥማትና ለሚነሱባት የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖትና ባህል ሳይገድባቸው በተባበረ ክንድ ጠላትን እያሳፈሩ ዳር ድንበሯን በማስከበር የጀግና ህዝብ መገኛ ምድረ-ቀደምት ሀገር እንደሆነች አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው።

አንድነት ሃይል ነው እንደሚባለው የአንድነትን ትርጉም ከኢትዮጵያኖች በላይ የሚረዳ የለም።

አንድ ሁነው ጠላቶቻቸውን በመመከት ሀገራቸውን ከቅኝ ገዥዎች በመጠበቅ ነፃነትን የሚቀዳጁና የሚሹ በመሆናቸው ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የኩራት ተምሳሌት በመሆን አድዋ ላይ ያስመዘገቡት ድል ሁሌም ሲዘከር እንዲኖር አስችሏል።

ሰሞኑን በክልላችን ጎንደር አካባቢ የተከሰተው ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ብጥብጥ አስነዋሪ ተግባርና ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻልና የአንድነት እሴት የሸረሸረ ነው።

ክልላችን ላይ ለብዙ ሺህ አመታት ተከባብሮና ተቻችሎ በፍቅርና በአንድነት የኖሩትን የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖቶችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከውጭና ከውስጥ የተደረገ የጠላቶቻችን ሴራ እንደሆነ የክልሉ መንግስት ይገነዘባል።

ጠላቶቻችን ከውጭም ከውስጥም በሚያደራጁትና በሚያቀነባብሩት ሴራ ባንዳዎችንና ተላላኪዎቻቸውን በገንዘብ በመደለል በመደበኛ ውጊያ ያልቻሉትን ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማቸው በሐይማኖት ውስጥ እየገቡ ማባሪያ የሌለው ሁከትና ጥፋት መፈጸም ይፈልጋሉ።

የሀይማኖት ግጭት በመፍጠር አንደኛው በአንደኛው ሀይማኖት ላይ ለጥፋት እንዲነሳ በማድረግ የዜጎች ህይወት እንዲጠፋና ጉዳት እንዲደርስባቸው ቤተ-እምነቶች እንዲወድሙ ቅርሶች እንዲጠፉ፣ የዜጎች ህይወት እንዲጠፋና ክልሉ የትርምስ ቀጠና ሆኖ ክልሉም ሆነ ሀገር እንዲፈርስ የተሄደበት ጽንፈኝነት በአጭሩ ካልተቀጨ አደገኛ እንደሆነ እንረዳለን።

የክልላችን ህዝብ የሚታወቅበት እሴቶቹ አንዱ የሀይማኖት መቻቻልና መከባበር ሲሆን የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖቶች አንዱ የአንደኛውን ቤተ-እምነት ሲያሳንጽና ሲገነባ የኖረ፣ አብረው ተረዳድተው ሲሰሩ የኖሩ፣ በዓላቶቻቸው በጋራ የሚያከብሩ፣ በደስታውም ሆነ በችግር አብረው የሚቆሙ መሆኑ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ልዩ ልዩ ቤተ-እምነቶች ትልቅ ኩራት የሚሆኑና ትምህርት የሚወሰድባቸው ትልቁ ማንነታችን ሆኖ ሳለ ከውስጣችን በሚበቅሉ የውጭ ጠላቶቻችን ተላላኪዎች ግጭት ጠማቂ በመሆን ሰላም ወዳዱን ህዝባችን እያመሡት ይገኛሉ።

በመሆኑም ሁሉም የክልላችን ህዝብ ለብዙ ሺህ አመታት የገነባነውን እሴቶቻችንና አኩሪ ባህላችን ጸንቶ እንዲዘልቅ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቻችን በገንዘብ ተገዝተው ሊያፈርሱን የተነሱትን ፅንፈኛ ሀይሎች ያለ ምህረት ሊታገላቸው ይገባል።

የክልላችን ህዝብ ያለምንም የሀይማኖትና የፆታ ልዩነት ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ መቋጫ የሌለው መሆኑን ተገንዝበን በተረጋጋ መንፈስና በአስተዋይነት አጥፊን በመለየትና ለህግ በማቅረብ ልንሻገረው ይገባል።

የክልላችን ወጣቶች የትኛውም ሀይማኖት ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርንና መደጋገፍን እንጅ ጥላቻንና መለያየትን አይሰብክምና እርስ በርሳችን ሊያባሉን የተነሱ የዘመናት ጠላቶቻችን በሃይማኖት ሽፋን ጽንፈኛ ሃይሎች የፈጠሩትን ግጭትና የደረሰውን ጉዳት ቆም ብሎ በማሰብ የተጎዳው ሁሉም አማራ መሆኑን፣ የተጠቀሙት ደግሞ ፅንፈኞች እንደሆኑ መረዳት አለብን።

ስለሆነም እነዚህ ፅንፈኞች በሚፈጥሩት ጥፋት ክልላችን ከአጀንዳ ላይ ሌላ አጀንዳ እየተቀበለ ከመደበኛ የልማት ስራዎቻችን እየወጣን ድህነትን እያባባስን ስለሆነ አሁን የተቃጣብንን አደጋ ያለምንም ልዩነት በፍፁማዊ ወንድማማችነት ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ ከክልሉና ከፌደራል የፀጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ሴራውን ልታከሽፉ ይገባል።

ወጣቶች የሃገር ተረካቢዎች ብቻ ሳትሆኑ ዋና ባለቤት በመሆናችሁ የክልሉን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ እንዲገነባ ለሰላም ትልቅ ዋጋ ልትሰጡ ይገባል።

ስለሆነም በየትኛውም መንገድ ፅንፈኝነትንና ፅንፈኛ ሃይልን በማውገዝ ወንጀለኛን በማጋለጥ የአካባቢያችሁን፣ የክልላችሁን፣ ብሎም የሃገራችሁን ሰላም ልትጠብቁ ይገባል።

በመሆኑም ሁሉም ወጣት ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ ሰላማችንንና አንድነታችንን በሚያውኩ ፅንፈኛ ሃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለክልላችን ዘብ ልትቆሙ ይገባል።

በክልላችን ውስጥ በየትኛውም መንገድ የህዝባችን ሰላምና አንድነት የሚያናጋ በሃይማኖትም ይሁን በሌላ ማናቸውም ዘዴ ግጭትን የሚሰብኩ፣ የሚቀሰቅሱና የፀጥታ መዋቅሩን ስራ የሚያደናቅፍ ማንኛውም አካልና ግለሰብ ላይ የክልሉ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን ያስገነዝባል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

ሚያዚያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም