የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፀረ ሠላም ኃይሎችና አጥፊዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

129

ሚያዝያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሠላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የፀረ ሠላም ኃይሎችና አጥፊዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች አሳስቧል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ‘በሐይማኖት ሽፋን የሚደረግ ጽንፈኝነት ተገቢነት የለውም!’ በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ አብሮነት መተባበርና መተጋገዝ እንደሀገር ያለን ኩሩ ሀብታችን ነው ሲል አስታውቋል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በሐይማኖት ሽፋን የሚደረግ ጽንፈኝነት ተገቢነት የለውም!ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ አብሮነት መተባባርና መተጋገዝ እንደሀገር ያለን ኩሩ ሀብታችን ነው።

ኢትዮጵያውያን በደስታቸውና በችግራቸው ያለ ልዩነት በጋራ ሲተባበሩ ዛሬን ደርሰዋል።

በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ያላስደሰታቸውና የግል ጥቅማቸው ተነካብን ብለው የሚያስቡ ቡድኖች የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ሰሞኑን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከኢትዮጵያዊነት እሴት ባፈነገጠ መልኩ የሀገራችን አንድነትና የህዝባችን አብሮነት የሚሽረሽሩ እንቅስቃሴዎች ተስተውለዋል።

የኢትዮጵያ የውስጥም ሆኑ የውጭ ጠላቶች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህንን እኩይ ተግባር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔራዊ መንግስት በጽኑ እያወገዘ ሠላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የፀረ ሠላም ኃይሎችና አጥፊዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡

በእምነትና በብሔር ሽፋን የሚገለጽ ጽንፈኝነት እንዳይዛመት መንግስት ከሠላም ወዳዱ ህዝብ ጋር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

የክልላችን ህዝብም የውጭ ጠላቶቻችን የሚያደርጉትን ሀገራችንን የማበጣበጥ አጀንዳ ተገንዝበው በየአካባቢያቸው ያለውን እንቅስቃሴ እንዲቃኙ፣ ከጸጥታ አካል ጋር እንዲተባበሩና ጥቅማቸውን ለማጋበስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን አውቆ እንዲታገሉ የክልሉ መንግስት ጥሪ ያቀርባል።

መላው ኢትዮጵያውያንም በብዙ መልኩ ተጋምዶ የኖረውን ሙስሊምና ክርስቲያን በደም ለማቃባት ብሎም ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን የፖለቲካ ሸፍጥ በአግባቡ ተገንዝቦ ይህን የሚመጥን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም