ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን መልካምነት በማስቀጠል ለሀገር ብልፅግና ሚናውን ሊወጣ ይገባል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

127

ሀዋሳ ሚያዚያ 23/2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን መልካምነት አጠናክሮ በማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ  ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች አንኳን 1443ኛውን ለዒድ-አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ደስታ በዚሁ መልእክታቸው  በተባረከው በረመዳን ወር የጀነት በሮች የሚከፈቱበት፤ የጀሀነብ በሮች የሚዘጉበት፤ ሰይጣን የሚታሰርበት ቅዱስ ወር  መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት ራሳችሁን ወደ ፈጣሪ  በቅድስና አቅርባችሁና አስገዝታችሁ የፆሙን ወር ፈፅማችሁ ለዒድ አልፈጥር በዓል በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል ።

ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት  ከመጥፎ ስራ የሚሸሽበት፤ ከወሬና ከሐሜት የሚርቅበት፤ ጤናማ ካልሆኑ ማንኛውም ግንኙነቶች ራሱን የሚያርቅበት፤ ስንፍናንና ሌሎች መጥፎ ባህሪዎችን በመቆጣጠር የፈጣሪ ትዕዛዝ እንዳይጥስ ራሱን በመንፈሳዊ ሥርአት የሚያለማመድበት የተቸገሩትን በመርዳት ፍቅርን የሚገልፅበት ወር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በፆም ወራት በሰደቃ ሰዎችን በገንዘብና በቁስ ከመርዳት ባሻገር በጉልበትና በእውቀት በማገልገል፤ በዘካ ዘልፈጥር ያጡትንና የተቸገሩትን ወገኑን በማብላትና በማጠጣት እንዲሁም ምንም ለሌላቸው ያለውን በመለገስ በማሳለፉ የክልሉ መንግስት ምስጋና ያቀርባል” ብለዋል።

“በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን መልካምነት በማጠናከር በቀጣይም ፈጣሪ ከማይወዳቸው ድርጊቶች እራሱን በማራቅ በኢትዮያዊ ጨዋነት ተሞልቶ ለሀገር ብልፅግና ሚናውን ሊወጣ ይገባል” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

ርእሰ መስተዳደሩ ለመላው እስልምና ሀይማኖት ተከታዮች በአሉ የሰላም እንዲሆን ተመኝተዋል።