በአማራ ክልል የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ

105

ሚያዚያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል 1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በየደረጃው ያለው የጸጥታ ኃይል በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት አድርጓል።

የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮችም ተቀናጅተው አካባቢያቸውን እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።

የክርስትና እምነት ተከታዮች የዒድ አልፈጥር በዓል የሚከበርባቸውን ቦታዎችና መስኪዶችን እያጸዱ መሆኑንና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ይገኛሉ ብለዋል።

በጎንደር ከተማ ሙስሊምና ክርስቲያኑ አንድ ሆነው በዓል የሚያከብሩበት እሴታቸውን ለመሸርሸር ያለመ በጥቂት ቡድኖች የተቀነባበረ ግጭት እንዲፈጠር መደረጉን አመልክተዋል።

“በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት የማንኛውንም እምነት የማይወክል ስለሆነ በሕዝቦች አብሮነት ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ አይችልም” ነው ያሉት  አቶ ደሳለኝ።

የገጠመንን ፈተና ማለፍ የሚቻለው በጋራ በመቆም ነው ያሉት ኃላፊው፤ ሕዝቡም ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ ይከበራል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም