ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በአልን የተቸገሩትን በመርዳትና የአብሮነት እሴትን በሚያጎላ መልኩ ማክበር አለበት

103

ሚያዚያ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በአልን የተቸገሩትን በመርዳትና የአብሮነት እሴትን በሚያጎላ መልኩ ማክበር አለበት ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ለ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፊጥር በአል የእንኳን አደረሳቹ መልእክት ዛሬ ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ያሳየውን በጎ ተግባር በኢድ አልፊጥር በአል በመድገም የተቸገሩትን መርዳት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዓሉን የአብሮነት እሴትን በሚያጎላ መልኩ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት ያለውን መልካምና በጎ ተግባራት በቀጣይነት መተግበር እንዳለበትም ገልጸዋል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ ኢድ አልፈጥር  ሲከበር ህዝቡ በጸጥታ ስራው ላይም አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በአሉ በሰላም እንዲከበር ከሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ከኢድ ማግስትም በሚከበረው ሹዋል ኢድ በዓል ላይ ህዝቡ የጀመረውን መልካም ተግባራት ዳግም ማሳየት እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።

ለ 1 ሺህ 443ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አል ፈጥር በአል የእንኳን አደረሳቹ መልእክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ በውጭ ሃገራት ለሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለሹዋል ኢድ በዓል ወደ ክልሉ እንዲመጡ  ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም