በቦዲቲ ከተማ ከ8 ሚሊዮንብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የኦክሲጂን ማምረቻ ስራ ጀመረ

141

ሶዶ፤ ሚያዚያ 22/2014 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ በአንድ ባለሀብት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ፕራይም ሜዲካል ኦክስጂን ማምረቻ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

ማምረቻውን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መና መኩሪያና የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ናቸው።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መና መኩሪያ በወቅቱ እንዳሉት የኦክሲጅን ማምረቻው  ለወላይታ ዞንና ለአጎራባች ለሚገኙ ጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በጎ አስተዋጾ አለው።

"ለድንገተኛ ህክምና ፈላጊዎች፣ ለጽኑ ህክምና ክትትል ለሚሹ ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ፈጣን የሆነ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል" ብለዋል።

የመተንፈሻ አካላት ህመም፣ ቀዶ ህክምናና ከሌሎች ከባድ ህመሞች ፈዋሽ ህክምና ለመስጠት የኦክስጅን ምርት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

በደንገተኛ አደጋና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኦክስጅን ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ባለመመጣጠኑ ይደርስ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

ማምረቻው በግል ባለሀብት ጥረት ለስኬት መብቃቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ለኦክስጂን አቅርቦት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማሰቀረት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የጤና ዘርፉን ለሚያግዙ በተለይም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን፣ ኦክስጅንና ሌሎች ተዛማጅ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማምረት ለሚሰሩ ሀገር በቀልና የውጭ ሀገር ድርጅቶች ልዩ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የቢሮው ምክትል ሃላፊ አስታውቀዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ የህክምና ተቋማት የኦክስጂን አቅርቦት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

ኦክስጅን ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ከሐዋሳና ሌሎች ከተሞች ለማምጣት የሚያጋጥመውን  እንግልትና ወጭ እንደሚፈታ አመልክተዋል ።

በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በዞኑ ማምረቻ ለሚገነቡ ባለሃብቶች ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የባለሃብቶችና የመንግስት ትብብር ወሳኝ በመሆኑ በቅርበት ድጋፍ በማድረግ ማምረቻው ወደስራ እንዲገባ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የቦዲቲ ከተማ ከንቲባ አቶ ታረቀኝ ባደቾ ናቸው።

የኦክስጂን ማምረቻው ባለቤት አቶ አስራት መኮንን የማምረቻው ጥናትና የግንባታ ሂደት የሁለት ዓመት ጊዜ የወሰደ መሆኑን ጠቁመው የማሽን ግዢው በአምስት ወር ተጠናቆ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ማምረቻው በቀን 120 ሲልንደር  የኦክሲጂን የማምረት አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።

ለማምረቻው ግንባታ ከ2 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ማግኘታቸውን ጠቁመው ከ100 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም