በጎንደር ከተማ በተፈጠረው ግጭት ተሳታፊዎችን ለመያዝ ሁሉም ነዋሪዎች ትብብር እያደረጉ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ

100

ሚያዚያ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በተፈጠረው ግጭት ተሳታፊዎችን ለመያዝ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር እያደረጉ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ግጭት የሁለቱንም ሀይማኖቶች የማይወክል የጥቂት ጸረ ሰላም ሀይሎች እኩይ ድርጊት ነው ብለዋል።

በግጭቱ የ15 ሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ላይም መጠነኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

የተከሰተው ግጭት  የሁለቱን ሀይማኖቶች የማይወክልና መፈጠር የሌለበት እንደሆነ በቁጭት መናገር የጀመሩት ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ለህግ እንዲቀርቡ ትብብር እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ370 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማን በማይወክለው አሳዛኝ ግጭት የተሳተፉ ጸረ ሰላም ሀይሎችን አድኖ የመያዝ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ተዘግተው የነበሩ አንዳንድ የከተማዋ ሱቆች ተከፍተው አሁን ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው፤ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እስከቀበሌ ድረስ ግልጽ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅ የሚያግዙ መመሪያዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።

በከተማዋ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለ ሲሆን ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ሀይሎች ውጭ ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይችልም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወደ ከተማ የሚገባ ማንኛውም ሰው የይለፍ መታወቂያ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት መከልከሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም