ጎንደርን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር በሃይማኖት ሽፋን የመጡ ነውጠኞችን መንግስት አደብ እንዲያሲዛቸው ተጠየቀ

107

ሚያዚያ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጎንደርን የግጭት ቀጠና ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገው አልሳካ ሲላቸው በሃይማኖት ሽፋን የመጡ ነውጠኞችን መንግስት አደብ ሊያሲዛቸው ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ግጭት የትኛውንም የሃይማኖት ተቋም እንደማይወክልም ነው የተናገሩት፡፡

በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ''አባ ለጋስ" በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁትን ሙስሊም አባት ስርዓተ ቀብር ለማስፈጸም የእስልምና፣ ክርስትናና ሌሎች እምነት ተከታዮች በተሰባሰቡበት ወቅት በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት መነሻነት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በከተማዋ ነዋሪዎች፣ በወጣቶች፣ በሀይማኖት አባቶችና በጸጥታ ሀይሎች ትብብር ሁከቱ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል፤ ጎንደርን የግጭት ቀጠና ለማድረግ የታሰበው ሴራም ከሽፏል።

ኢዜአ በጎንደር ከተማ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የእስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተከሰተው ግጭት በጎንደር ከተማ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ እንግዳ ነገር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጎንደር ሙስሊሙ ክርስቲያን እህትና ወንድም፤ ክርስቲያኑ ደግሞ ሙስሊም እናትና አባት ያለው ህዝብን የያዘች ከተማ መሆኗንም ነው የተናገሩት።

ቤተክርስቲያን ሲሰራ ሙስሊሞች አግዘው መስጊድ ሲገነባ ክርስቲያኖች ተባብረው በመስራት የሃይማኖት መቻቻልና አንድነት የሚሰበክባት የሰላም ከተማ ሆና ዓመታትን አሳልፋለች ብለዋል።

ከሰሞኑ የሀይማኖት ቅርጽ እንዲኖረው ታስቦ የተሸረበው ሴራ ለማንኛውም የእምነቱ ተከታይ እንግዳና አስደንጋጭ እንደነበር የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ ድርጊቱ በወሰንና በብሔር ማንነት ያልተሳካውን ሀገር የመበጥበጥ እኩይ ዓላማ በሀይማኖት ለመሞከር የታሰበ ነው ብለዋል።

በጎንደር ከተማ በክርስትናና እስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ለዘመናት የዘለቀውን አንድነት ጥላሸት ለመቀባት የተቀነባበረው ሴራ የሁለቱንም እምነት ተከታዮች እንደማይወክል ጠቁመዋል።

በድርጊቱ እጃቸው ያለበት አካላት ለህግ እንዲቀርቡ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች የህዝብን አብሮነት የማይፈልጉ አካላትን ሴራና ተንኮል ተገንዝበው ምዕመናንን በስነ-ምግባር ማነጽ እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ "ያልሆነውን ሆነ ያልጠፋውን ጠፋ" እያሉ በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ገልጸዋል።

መንግስት በማህበራዊ ድረ ገጾች ሽብር የሚነዙ የግጭት ጠማቂዎችን አደብ እንዲያስገዛቸውም ጠይቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ በኢትዮጵያ ግጭትን የሚያባብሱ ኃይሎች እየተበራከቱ መሆኑን ተገንዝቦ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሃይማኖት አባቶችና ወላጆች ትውልድ የማስተማር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ መንግስት ህግ የማስከበር ግዴታውን በሚጠበቀው ልክ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም