የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት የሀገር አፍራሾችን ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል

81

ደሴ ሚያዚያ 22/2014 (ኢዜአ ) 'ኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት የሀገር አፍራሾችን ሴራ በጋራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል'' ሲሉ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እስሌማን እሸቱ አስገነዘቡ ፡፡

ነገ የሚከበረውን የዳግም ትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በደሴ ከተማ ለ5 ሺህ አቅመ ደካሞችና ችግረኛ ተማሪዎች  የማእድ ማጋራት ስነ ስርአት ዛሬ ተካሂዷል።  

ምክትል ከንቲባ አቶ እስሌማን እሸቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰሩ ቢሆንም በኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት እየከሸፈ ነው፡፡

"በተለይ አንድ ሆነን እንዳንቆም በብሄርና በእምነት ለመከፋፈል ጥረት ቢያደርጉም ባለን ጥብቅ ትስስርና ድንቅ ባህል ሊሳካላቸው አልቻለም" ብለዋል፡፡

"ጠላቶቻችን አሁንም መልካቸውንና ስልታቸውን እየቀያየሩ በሚያደርጉት ሙከራ መታለል የለብንም" ሲሉ አክለዋል፡፡

"የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት የአገር አፍራሾችን ሴራ በጋራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

"የማእድ ማጋራት የምሳ ግብዣው አንድነታችንና የመረዳዳት ባህላችንን ለማጠናከር ያግዛል" ሲሉም ከንቲባው  አስታውቀዋል።

"ወቅቱ አንድነታችንና ሰላማችንን ከምንጊዜውም በላይ በጋራ ጠብቀን ኢትዮጵያን የምንታደግበት ነው" ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት ሲራክ መለሰ  ናቸው።

"እንደየ እምነታችን ፀሎት በማድረግ፣ ሰላምና አንድነትን በመስበክ ትውልዱ በጋራ አገር እንዲጠብቅ ማድረግ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር የማእድ ማጋራት የምሳ ግብዣው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም