ከ"ኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት" ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የዳያስፖራ አባላት በኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ ለልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋገጡ

184

ሚያዚያ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ ለአገር ልማት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ከ "ኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት" ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የዳያስፖራ አባላት ተናገሩ።

ወደመጡበት አገር ሲመለሱ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በማስረዳትና በአገሪቷ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ከ "ኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት" ጥሪን ተቀብለው ወደ አገርቤት ከገቡ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳያስፖራ አባላት በቆይታቸው ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ አገር መሆኗን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቱርክ እንደመጡ የተናገሩት አቶ ሁሴን ናስር ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ይናገራል፡፡

በቀጣይ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ተናግረው፤ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያለው ምቹ ሁኔታ መዋለንዋያቸውን ለማፍሰስ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

በኳታር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ቀጸላ በበኩላቸው፤ በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ በበርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመለየት በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ችግራችንን በራሳችን አቅም መፍታት አለብን ያሉት አቶ ቁምላቸው፤ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በመለየት ወደ መጡበት ሲመለሱ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ወደ መጣንበት አገር ስንመለስ  የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በማስረዳት ረገድ በትኩረት እንሰራለን ያሉት ደግሞ ከሳውዲ አረቢያ የመጡት አቶ አብዱላዚዝ ኡመር ናቸው፡፡

ሌላው ከሳውዲ አረቢያ የመጡት አቶ ሳላህ መሐመድ፤ "በተመለከትኩት ነገር ተደስቻለሁ፤ ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በልማት እንዲሳተፉ የበኩሌን አደርጋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም