የፊቼ ጨምባላላን የመደማመጥ፣ የመከባበርና የይቅርታ ጥበብ ለሀገራዊ ምክክር መጠቀም ይገባል

93

ሀዋሳ ሚያዚያ 222014(ኢዜአ)...የፊቼ ጨምባላላን የመደማመጥ፣ የመከባበርና የይቅርታ ጥበብን ሊካሄድ ለተወጠነው ሀገራዊ ምክክር በመጠቀም ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል የደቡብ ክልል የቀድሞ ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

በሃዋሳ ትናንት በተከበረው የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል ላይ የታደሙ  የደቡብ ክልል የቀድሞዎቹ ርዕሳነ መስተዳድር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤና አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የቀድሞዎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች በሰጡት አስተያየት ፊቼ ጨምባላላን የመደማመጥ፣ የመከባበርና፣ የይቅርታ ጥበብ ለሀገራዊ ምክክር በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ለመላው የሲዳማ ህዝብ "አይዴ ጨምባላላ" መልዕክት ያስተላለፉት አምባሳደር ሽፈራው፤ በዓሉ እንደ ሀገር እያለፍንበት ላለው አስቸጋሪ ሁኔታ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የሲዳማ አባቶች ፊቼ ጨምባላላ ከመከበሩ አስቀድመው በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ ችግሮችን ተነጋግሮ የመፍታትና መፍትሄ የማስቀመጥ ጥበብ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሂደት የመደማመጥ፣ የመከባበርና እውነት የማምጣት አቅም እየጎለበተ ይሄዳል ያሉት አምባሳደር ሽፈራው፣ የአባቶችን የችግር አፈታት ስልት ሀገር ለገጠማት ፈተና መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ተያይዘው የመጡ የተለያዩ ትርክቶችን በማጥራት አንድነትን ለማጠናከርና ከችግር ለመውጣት ሚና ላለው ሀገራዊ ምክክር፣ በፊቼ ጨምባላላ እሴቶች ውስጥ ያለውን ጥበብ መጠቀም ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

አባቶች በራሳቸው የችግር አፈታት ሥርዓት ሀገር እየመሩ ለዚህ ትውልድ ማድረሳቸውን የገለጹት አምባሳደር ሽፈራው፣ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ እሴቶቹን መጠበቅና ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ፊቼ ጫምባላላ ያሉ ጠቃሚ ባህሎች በአካባቢ ሳይወሰኑ በሌሎችም ዘንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ሀገራዊ ሚናቸውን ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ዴኤታና የቀድሞ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ፊቼ ጨምባላላ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው እሴቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ የመረዳዳት፣ የመከባበርና የእርቅ እሴቶችን በውስጡ መያዙን ጠቅሰው፣ የብዝሃነት ማሳያም መሆኑም አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም እንደ ሀገር በአንድነታችን ላይ እያጋጠመን ያለውን ችግር ለመፍታት የይቅርታን ጠቃሚነት ከፊቼ ጫምባላላ እሴት መውሰድ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗን ያነሱት አቶ ሚሊዮን፣ ትልቅ ሀገር ለመገንባት ከሀገር በቀል እውቀቶች ልምድ መቅሰም ይገባል ብለዋል፡፡

ይቅርታ አድራጊ ህዝብ መሆን ትልቁና ከበዓሉ የምንወስደው እሴት መሆኑን ገልጸው፤ ያለፉ ችግሮቻችንን መፍታትና ይቅርታን ለሀገራዊ ምክክር በማዋል ''ወርቃማውን ዕድል'' መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር የገጠሙን ችግሮች የሚፈቱት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግና በመደማመጥ  በመሆኑ የቀደምት አባቶችን ጥበብ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ፊቼ ጫምባላላ ከሰባት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም