የሴቶችን የሀብት እድገትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ዳግም መቃኘት ያስፈልጋል-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

112

አዳማ ሚያዝያ 22/2014/ኢዜአ/ የሴቶችን የምጣኔ ሀብት እድገትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን  ዳግም  መቃኘት እንደሚያስፈልግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአዳማ ከተማ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሴቶች የኢኮኖሚ ፎረም ምስረታ ጉባኤ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ አቦንግ የሴቶች የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚፈለገው መልኩ እየሄደ አይደለም ብለዋል።

በተለይ ሴቶችን በኢኮኖሚ ከማብቃትና በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ውስንነትና ተግዳሮቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በእርሻና አካባቢ ጥበቃ ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትናና ኢንቨስትመንት፣ በመሬት ባለቤትነት፣ በምርትና በሃብት ባለቤትነት ዙሪያ የሴቶች ድርሻ ከወንዶች አንፃር ሲታይ አሁንም ሰፊ ልዩነትና ክፍተት የሚታይበት መሆኑን ጠቁመዋል ።

"ክፍተቱን ለመሙላት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል" ያሉት ወይዘሮ አለሚቱ "በዋነኝነት የሴቶችን የምጣኔ ሀብት እድገትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን   ዳግም  መቃኘት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ሀገር አቀፍ የሴቶች የኢኮኖሚ ፎረም መመስረት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው  ፎረሙ ሴቶች በኢኮኖሚ እንዲጎለብቱ ከማድረግ አንፃር በዘላቂነት የሚሰራ ጥምረት መሆኑን ተናግረዋል።

"ፎረሙ የሴቶች የኢኮኖሚ አቅምና ብቃት እንዳይጎለብት መሰናክል የሆነባቸውን ማነቆዎች በጥናት በመለየት ዘላቂ መፍትሄ፣ የማስፈፀሚያ ስልቶችና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ጭምር የሚሰራ ነው" ብለዋል።

በስራና ክህሎት ሚኒስቴር  የስራ ፈጠራ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው "በቀጣይ አስር ዓመት የዘርፉ የልማት እቅድ የሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ምጣኔ ከወንዶች እኩል 50 በመቶ ለማድረስ ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታተ በዘርፉ አበረታች ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም በሴቶችና በወንዶች መካከል የስራ እድል ፈጠራ ፍትሃዊነት ላይ ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል።

እስካሁን የሴቶች የስራ እድል ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ምጣኔ 36 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ በሀገሪቱ ከሚፈጠረው አጠቃላይ የስራ እድል ውስጥ 64 በመቶ የሚሆነው በወንዶች የተያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

የሴቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ምጣኔ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ  ጥረት የሚያስፈልግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የዩኤን ውሜን በኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስ አና ሙተቫቲ በበኩላቸው የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ተሳትፎን ለማረጋገጥ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

"በተለይ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ሴቶች ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት  በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን ለማገዝ የተነደፈው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ግቡን እንዲያሳካ በትብብር እንሰራለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም