ከ1ነጥብ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ አበባ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሊያካሂድ ነው

73
አዲስ አበባ ጳጉሜን 2/2010 የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በ1 ቢሊዮን 326 ሚሊዮን ብር ወጪ የአዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችና የመንገድ ጥገና ስራ ሊያካሂድ መሆኑን ገለጸ። ወጪው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን መሆኑንም ባልስልጣኑ አስታውቋል። ባለስልጣኑ ግንባታውን ከሚያካሂዱ፣ የማማከር እንዲሁም የዲዛይን ጥናት ስራ ከሚያከናውኑት አማካሪ ድርጅቶችና ስራ ተቋራጮች ጋር የስምምነት ውል ተፈራርሟል። በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ስድስት የስራ ተቋራጮችና አምስት አማካሪ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን የአዲስ መንገድ ግንባታውና ጥገናው ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ እንደሆነ ተጠቁሟል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በስምምነቱ ላይ እንደገለጹት፤ የከተማውን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ዲዛይን የሚሰራላቸውን መንገዶችን ለይቶ የቅድመ ዝግጅትና የዲዛይን ጥናቶችችን እያከናወነ ይገኛል። ይሰራል ተብሎ የውል ስምምነት ከተፈጸመበት ፕሮጀክት መካከል የ25 ነጥብ 32 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፓልት ኮንክሪትና የጠጠር መንገድ ግንባታ ይገኝበታል። 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታ ስራ የሱፐርቪዥን እና የማማከር እንዲሁም 156 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የመንገድ ዲዛይን ጥናት ስራዎች በከተማ አስተዳደሩ ወጪ እንደሚከናወኑ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ስራ ተቋራጮችም ስራቸውን በጥራት በተያዘላቸው ጊዜ ሰርተው ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው ኢንጅነር ሞገስ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም