ኢትዮጵያ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለድርቅ ተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ የልማት አጋሮች ድጋፍ ያስፈልጋታል

88

ሚያዚያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለድርቅ ተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ዩኒሴፍ በበኩሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ለተከሰተው ድርቅ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሃብት ማሰባሰብ ስራ እሰራለሁ ብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል ጋር በጽህፈት ቤታቸው ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረጋቸው ባሉ የልማትና የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች ዙሪያ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕፃናት፣ በትምህርት፣ ጤናና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራዎች ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለ የልማት አጋር እንደሆነ ገልጸዋል።

“በኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ብዙ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል፤ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎች  ትምህርት፣ ጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ አድርጓል” ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅም በኢትዮጵያ ውስጥ በሰዎችና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝና መንግስት የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ እንዲሁም አደጋውን ለመከላከል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለድርቅ ተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እንደ ዩኒሴፍ ያሉ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል በበኩላቸው መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው መስኮች ላይ ድርጅታቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነው ብለዋል።

በቀጠናው የተከሰተው ድርቅ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ባሉ ግጭቶች ተሸፋፍኖ ትኩረት እንዳያጣ በማሰብ በአፍሪካ ቀንድ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለድርቁ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ ለተጎጂዎች አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ሃብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በግጭትና የተፈጥሮ አደጋ ይበልጥ ሕፃናት ተጎጂ መሆናቸውንና ዩኒሴፍ ጉዳቱን ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግስት ለሚያደርጋቸው ጥረቶች  የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የሚገኙት የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴና ከአፍሪካ ሕብረት ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳናዛባጋንዋ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

ዋና ዳይሬክተሯ ወደ ሶማሌ ክልል በማቅናት ድርቅ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች የጎበኙ ሲሆን፤ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ጋር በድርቅ ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የዳይሬክተሯ የጉብኝት ዓላማ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ሕጻናትን ሁኔታ በቦታው ተገኝቶ ለማየትና ለመርዳት የሚያስችላቸውን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማስገኘት እንደሆነ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም