የሐረሪ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር የተፈጸመውን የጥፋት ተግባር አወገዘ

87

ሐረር ፤ ሚያዝያ 20/2014(ኢዜአ) የሐረሪ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን  የጥፋት ተግባር አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታወቀ።

ጉባዔው ባወጣው መግለጫ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን ህገ ወጥ ድርጊት ኮንኗል።

ሰላም ወዳዱን ህዝብ  በኃይማኖት ሽፋን ለማጋጨት የሚደረገው ሴራ የትኛውንም ኃይማኖት የማይወክልና ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቋል።

''በህዝቦችና በኃይማኖቶች መካከል ለዘመናት ዘልቆ የኖረውን ትስስርና አብሮነት ለመናድ የሚደረግ አስተሳሰብና ድርጊት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ኃጢያታዊ ተግባር ነው'' ብሏል የክልሉ  የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ  በመግለጫው።

ተግባሩም በጎንደር ከተማ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነትና ተከባብሮ የመኖር እሴትን ለመሸርሸር ታልሞ የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ እንደሚቃወመው ገልጿል።

ድርጊቱን የፈጸሙና የተሳተፉ አካላት ክትትል ተደርጎ ለህግ እንዲቀርቡም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም