ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ለምታከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል --የጃፓን አምባሳደር

101

ሀዋሳ ሚያዝያ 20/2014 (ኢዜአ) ጃፓን ኢትዮጵያ በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ መስኮች ለምታከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር አስታወቁ።

በጃፓን መንግስት በተገኘ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ የተገነባ ዩዎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካካኦ በትምህርት ቤቱ ምረቃት ስነስርዓት ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያና ጃፓን በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ እየሰሩ ነው።

በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1989 ዓም ጀምሮ ባለፉት 33 ዓመታት ኤምባሲው በኢትዮጵያ በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ መስኮች 400 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አመልክተዋል።

በትላንትናው እለትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በቤት አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ አጠናቆ ማስመረቁን ጠቁመው ትምህርት ቤቱ  እያንዳንዳቸው አራት የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው ሁለት ብሎክ ህንጻዎች ያሉት መሆኑን ተናግረዋል ።

ግንባታው በትምህርት ቤቱ ያለውን የክፍል ጥበት በማቃለል ተጨማሪ 200 ተማሪዎችን ለማስተማር እንደሚያስችል ጠቅሰው የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችም የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት በማደግ በአሁኑ ሰዓት እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት እንደሚሰጥበት ተናግረዋል።

"በኛ ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት በእግር እየተጓዝን ውጤት ማምጣት ከቻልን በአሁኑ ሰዓት ያሉ ተማሪዎች በቅርበት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው መማራቸው የበለጠ ውጤታማ መሆን ያስችላቸዋልና በትጋት ትምህርታቸውን መማር አለባቸው" ብለዋል።

ጃፓን ለከፍተኛ ዕድገትና ስልጣኔ ደረጃ ያበቃት በትምህርት ላይ በትኩረት በመስራቷ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ተማሪዎች በትምህርታቸው በርትተው ስኬታማ ለመሆን መጣር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ግንባታው በትምህርት ቤቱ ያለውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለማቃለልና የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሶ ናቸው።

በትምህርት ቤቱ ከመቶ በላይ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚማሩ አስታውሰው አዲስ የማስፋፊያ ግንባታው የተማሪ ክፍል ጥመርታውን እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም