ህዝበ ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ አብሮነቱን ፣ሠላምና ፍቅርን አጠናክሮ መቀጠል አለበት

143

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 19/2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ አብሮነቱን ፣ሠላምና ፍቅርን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የሲዳማ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ሙስጠፋ ናስር አሳሰቡ።

በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች  የተሳተፉበት የጎዳና ላይ የ"አፍጢር" መርሃ ግብር ትናንት ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ  ተካሂዷል።

በዚህ ውቅት ሀጂ ሙስጠፋ  እንደተናገሩት፤ ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ፆምን ለፈጣሪው በመገዛት፣ በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ እያሳለፈ ይገኛል።

የጎዳና ላይ አፍጥር መርሃ ግብሩም የዚህ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ያጎለበተውን ኢትዮጵያዊ  አብሮነት ፣ ሠላምንና መዋደድን እንዲሁም ያለው ለሌለው የማካፈል  ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሀጂ ሙስጠፋ አሳስበዋል።

የሀዋሳ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጂ ቃሲም ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ ረመዳን የተለየ የእዝነትና የራህመት ወር ነው ብለዋል።

የከተማው ሙስሊሙ ማህበረሰብ  ለሠላም ዘብ በመቆም የረመዳን ወርን በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ እንዲያሳልፈው ጠይቀዋል።

የመረሃ ግብሩ ተሳታፊ ሼህ ጀሚል አደም በበኩላቸው፤ በርካታ ሙስሊም እህት ወንድሞች የተሳተፈበት የጎዳና ላይ ´´የአፍጢር´´ መርሃ ግብር ታሪካዊ  መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ለመንግሥት ምስጋና አቅርበዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በመረሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማህበረሰቡ  በረመዳን ወር የሰራቸውን መልካም ተግባራት ከዕለት ዕለት ማሕበራዊ ሕይወቱ ጋር ሊያቆራኘው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ከሌላውም ጋር አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር ለሀገር ሠላምና ብልጽግና እንዲተጋም ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም