ልሳነ ብዝሀነትን ማበረታታትና መደገፍ - የአገራዊ ልማት አንዱ መስመር 

403
ቋንቋ ከመግባቢያነት ባለፈ የተናጋሪው ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ ነው። በዓለም ዙሪያ ከ6 ሺህ በላይ የሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገለጫ የሆኑ ቋንቋዎች እንዳሉ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ በሰፊው ከሚነገሩ ቋንቋዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ማንዳሪን፣ እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ሂንዲ፣ አረብኛ፣ ቤንጋሊ፣ ራሺያን፣ ፖርቱጊዝ፣ ጃፓኒክ፣ ጀርመንኛ እና ፈረንሳይኛ ናቸው።
ኢትዮጵያም ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ልሳነ ብዙ አገር ናት። በአገሪቱ አፍሮ-እስያዊ እና ናይሎ ሳህራዊ የሚባሉ ሁለት ትልቅ የቋንቋ ቤተሰቦች ወይም ክፍሎች አሉ። በአፍሮ- እስያ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ስድስት የሚሆኑ ንዑስ የቋንቋ ቤተሰቦች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ኩሻዊ፣ ኦሞአዊ እና ሴማዊ በኢትዮጰያ ይነገራሉ።
ከነዚህ ውስጥ ኦሞአዊ ቋንቋዎች በኢትዮጰያ ብቻ ሲገኙ ኩሻዊ ቋንቋዎች በኢትዮጰያና አጎራባች አገሮች ይነገራሉ። ሴማዊ ቋንቋም በአገራችን የሚነገር ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንደሚነገር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በተፃፈ ህግ፣ አማርኛ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረጋቸው ይነገራል። አማርኛን ይፋዊ የስራ ቋንቋ ያደረገው የንጉሥ ነገስቱ ስርአት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች የሬዲዮ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጐም እንደነበር ይጠቀሳል፡፡
ወቅቱም የቋንቋ ብዝሃነትን ማስተናገድ የተጀመረበት ነበር ማለት ይቻላል፤ ኋላም በደርግ ዘመነ መንግስት 15 የሚደርሱ ቋንቋዎች ለመሠረተ ትምህርት ማስተማሪያነት እንዲውሉ መደረጉን የታሪክ ደርሳናቱ ያትታሉ። በነዚህ ቋንቋዎች  ምርምር ያካሂድ የነበረው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚም፣ ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ጥናት አካዳሚነት አድጐ የተለያዩ ጥናቶችን አድርጓል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የጠራና ግልጽነት ያለው የቋንቋ ፖሊሲ ሳይኖራት ቆይታለች።

በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት፤ ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል እውቅናን የሠጠ ህገ-መንግስት የተደነገገ ሲሆን ቋንቋዎችን ለትምህርትና ለስራ የመጠቀም ተግባርም ተከናውኗል፡፡ ከ50 በላይ ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋ መሆን ችለዋል፡፡ ክልሎችም የየራሳቸው የስራ ቋንቋዎችን መርጠው እንዲጠቀሙ ማድረግም እንዲሁ።

የቋንቋና የስነ-ቃል ምሑሩ ዶክተር አውላቸው ሹምነካ ክልሎች ቋንቋቸውን የትምህርት፣ የሥራና የሚዲያ አድርገው መጠቀማቸው የቋንቋ እድገት ማሳያ ነው ይላሉ። ነገር ግን ቋንቋዎች በአግባቡ ተመርጠው ለትምህርት፣ ለስራና ለብሔራዊ መግባባት የሚውሉበት ጠንካራ የአሰራርና የአመራር ስርአት አልነበረም፡፡ በዚህም ቋንቋዎችን ለማበልፀግም በቂ ርቀት መጓዝ አለመቻሉን ይናገራሉ።

ህገመንግስቱ ካስቀመጠው የቋንቋዎች እኩልነት ባለፈ ዝርዝር የሆነ የቋንቋ ፖሊሲ ባለመኖሩ ክልሎች በመሰላቸው መንገድ ይሄዱ እንደነበር የሚገልጹት ምሁራኑ ይህ አይነቱ ያልተደራጀ የቋንቋ አጠቃቀም ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመስራትና የመግባባት መብታቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልሳን ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሞገስ ይገዙ፤ በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማትን የሚመራ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ ቋንቋዎች በሚፈለገው ደረጃ እድገት ሳያስመዘግቡ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ቋንቋዎቹ በስርዓት ባለመመራታቸውና በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ልዩነታችንን የሚያሰፉና ለግጭትም ጭምር መንስኤ ሲሆኑ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ባለመፍጠሯ ችግሮች እያየሉ መምጣታቸው ይታመናል። በአዋጅ ስልጣን የተሰጠው የቋንቋ አካዳሚ ባለመኖሩና ፖሊሲን መሰረት ባደረገ መልኩ በጥናትና በእውቀት ላይ በመመስረት ቋንቋን በአግባቡ መምራት አለመቻሉ ደገሞ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በዚህም ቋንቋዎች በሚፈለገው ልክ ማደግ አልቻሉም።

ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ የቋንቋ ፖሊሲ አጽድቃለች። ፖሊሲው ለአገሪቱ ቋንቋዎች እድገትና ልማት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ምሁራን ይናገራሉ። የቋንቋ ፖሊሲው የፌዴራል ስርዓቱን የበለጠ የሚያጠናክር እና በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን በአደረጃጀት የሚመልስ እንደሆነም ይታመናል። ፖሊሲው የብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ የሚፈጠርበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል። ከቋንቋዎች ጋር በተገናኘ በአጠቃቀም፣ ጥበቃና ልማት ረገድ የሚነሱ ጥያቄዎች የሚፈቱበት እንደሆነ ያስረዳሉ። አገራዊና ቀጠናዊ አንዲሁም አህጉራዊና አለማቀፋዊ ትስሰር ለማሳለጥም የሚጠቀም እንደሆነ ይናገራሉ። ትኩረት ያላገኙና በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎች ስርዓታዊና ተቋማዊ እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግና ባህላዊ እሴቶችና ዕውቀቶች ለትውልዱ የሚተላለፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድም ፖሊሲ መኖሩ ወሳኝ እንደሆነ ይስማማሉ።

ፖሊሲው በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን ስርዓት የማስያዝ ዓላማ ያለው ሲሆን ለተፈጻሚነቱ ይረዳ ዘንድም በቅርቡም የጥናትና የትርጉም ተቋም ለማቋቋም ደንብ ተዘጓጅቷል። ከአማርኛ በተጨማሪ አራት ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ፖሊሲው ያስቀመጠ ሲሆን እነዚህም ኦሮሚኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሌኛና ትግሪኛ ናቸው። ቋንቋዎቹ የተመረጡት ከሚነገሩበት ክልል በዘለለ በጎረቤት አገሮች ጭምር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው በመሆኑ፣ ከአማርኛ ቋንቋ ጎን ለጎን ጥቅም ላይ ቢውሉ ልሳነ ብዙ አገረ መንግሥት ከመገንባት ባሻገር ውስጣዊና ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያፋጥን ስለታመነበት ነው።

እነዚህ ድምበር ዘለል ቋንቋዎች ከጎረቤት አገራት ጋር ኢኮኖሚክ ኢንተርግሬሽን ለማምጣት ያግዛል። የንግድና ዲፕሎማሲ ግንኙነታችንን ለማሳለጥ፣ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን  ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። ልሳነ ብዙ መሆን ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፤ እንዲያውም ሃብት ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ። ይህም በፖሊሲ መደገፉ ደግሞ ትልቅ እመርታ መሆኑን በመጥቀስ የቋንቋ በተለይ ከታች ጀምሮ ትኩረቱን ልጆች ላይ በማድረግ ከተሰራ ጠቀሜታው ጉልህ እንደሚሆን ይናገራሉ።

ሁለትና ከዚያ በላይ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ኢትዮዽያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም። በመሆኑም ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች የሥራ ቋንቋዎችን መጠቀም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ተግባቦትን ለማሳለጥ አንዱ መንገድ ነው ይላሉ ምሁራኑ። ቋንቋዎች ለትምህርት፣ ለንግድ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ስርጸት፣ ለባህልና ለስነ-ጽሁፍ እድገት በአጠቃላይ ለዘመናዊ ሰልጣኔ መሸጋጋርያና ለዲፕሎማሲ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው።

የቋንቋ ብዝሀነት አያሌ ትሩፋቶች አሉት። በተለይ ትምህርትን ለማዳረስ ዓይነተኛ መንገድ ነው። ለምሳሌ ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለማዳረስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። ምክንያቱም ማንኛውም ህጻን በሚገባውና በሚያውቀው ቋንቋ መሰረታዊ የሆነውን ትምህርት ማግኘት አለበት። ኢትዮጰያም የዩኔስኮን ሀጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው የሚል ድንጋጌ ተቀብላ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

ቋንቋዎችን የማልማትና የማሳደግ ዝንባሌ በአገሪቱ እያደረገ መምጣቱን የሚገልጹ ምሁራን ልሳነ ብዙ የሆኑ አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ከፖሊሲው ጋር አጣጥሞ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ። በአለም ላይ ልሳነ ብዙ የሆኑ አገራት ብዝሃነታቸውን እንዴት እያስተናገዱ እንደሆነ ከህንድ፣ ኢንዶኔዢያና ሌሎች አገራትን ተሞክሮ  መውሰድ ጠቃሚ ነው ይላሉ።

ህንድ ህብረ ብሔራዊና ልሳነ ብዙ አገር ናት። በአገሪቱ ከ1ሺ በላይ ቋንቋዎች አሉ። እንግሊዝኛ እና ሂንዲ ቋንቋዎች የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች ናቸው። ሁሉም ክልላዊ መንግስታት የራሳቸውን ቋንቋ ይጠቀማሉ። በትምህርት በኩል ደግሞ እንግሊዝኛ እንደ መጀመሪያ ቋንቋ ይሰጣል። ሌሎች ሁለት ቋንቋዎች ሰው የፈለገውን መርጦ እንደ ክልሉ ሁኔታ ደግሞ እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ቋንቋ ይሰጣል። በአጠቃላይ አንድ ተማሪ ከኬጂ ጀምሮ ቢያንስ ሶስት ቋንቋዎች ይማራል። በፖሊሲ የሚመራው ቋንቋቸው ለግጭትና ላለመስማማት መንስኤ ምክንያት ሲሆን አይታይም።

ደቡብ አፍሪካ ሌላዋ ምሳሌ መሆን ትችላለች። እ.ኤ.አ. በ1996 ተሻሽሎ የፀደቀው የአገሪቷ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ከሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች መካከል አስራ አንዱን የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ አድርጓል። ይህንን ኢትዮጵያ እንደ ጥሩ ተሞክሮ ልትወስደው ይገባል የሚሉ በርካታ ናቸው።

በርካታ ቋንቋዎችን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ማድረግ ክልሎች ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋን እንዲጠቀሙ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ቋንቋዎች የአገልግሎት አድማሳቸው እንዲሰፋ በማድረግ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት ያስፈልጋል።

የቋንቋዎች እድገት የህብረተሰቡን አብሮነት የሚያጎለበት ከመሆኑም ባለፈ አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅሞ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እድል ስለሚሰጥ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በተሻለ ጥቅም ላይ ለማዋል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው።

የፖሊሲው ዋና ዓላማ የቋንቋ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ መተግበር፣ ልሳነ ብዝሀነትን ማበረታታት፣ በቋንቋ ዙሪያ የሚያጋጠሙ ችግሮችን መፍታትና የቋንቋ ልማትን በሥርዓት መምራት መሆኑን በመገንዘብ ለተፈጻሚነቱ መረባረብ ወሳኝ ነው። የቋንቋዎች ልማት ለአገራዊ ልማት ወሳኝ ከሆኑ መንገዶች መካከል አንዱ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ፖሊሲውን ተቋማዊ ለማድረግም ብሄራዊ የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት፣ የቋንቋዎች ጥናት ማዕከሎች፣ እና የትርጉም ተቋም መመስረት አስፈላጊ በመሆኑ የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል ያሻል። ማህበራዊው፣ ኢኮኖሚያዊው፣ ባህላዊውና ፖለቲካዊው የሀገር ጉዳይ ሁሉ ካለቋንቋ የሚከወን ባለመሆኑ የቋንቋ ጉዳይ በግለሰብ፣ በማህበረሰብና በመንግስት ዘንድ እንደሌሎች ጉዳዮች በቀላሉ አይታይም፤ መታየትም የለበትም። ዜጎችን ልሳነ ብዙ የማድረግ ጅማሮም ለአገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም