የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ብድር ጋር የተያያዘ ማሻሻያ ሊያደርግ ነው

164
አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ ለሚሰጠው ብድር በተለየ ሁኔታ የወለድ መጠኑና የእፎይታ ጊዜው ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቻይና እና ኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የብድር ክፍያ እፎይታ ጊዜን ለማራዘምና የወለድ መጠንን ለመወሰን የሚያስችል ስምምነት ከቻይና መንግስት ጋር ተደርጓል። ከዚህም ሌላ በአገሮቹ መካከል ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ድጋፍ ከብድር ይልቅ ወደ እርዳታ የሚያተኩርበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ከስምምነት  ላይ መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል። በአጠቃላይ በቻይናና ኤርትራ የተደረገው ጉብኝት ስኬታማ እንደነበርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። በቻይና እና አፍሪካ የትብብር ፎረም የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቻይና መንግስት ለአፍሪካ አገሮች የ60 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ ማድረጉን  ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ "ከዚህ ፈንድ ውስጥ የተሻለ ድርሻ እንዲኖራት ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅባታል" ብለዋል። ከጉባዔው ጎን ለጎን ደግሞ ከቻይና መንግስትና ሌሎች አገሮች ጋር የተደረገው የሁለትዮሽ ምክክሮሽም ስኬታማ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተለይ ከቻይና መንግስት ጋር በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ከአገሪቷ የወሰደችውን ብድር አከፋፈልና የንግድ ልውውጡን ሚዛን ለማስተካከል የተደረገው ምክክር ተጠቃሽ መሆኑን ነው ያወሱት። በዚህም የብድር ክፍያ እፎይታ ጊዜውን ለማራዘም፣ የወለድ መጠንን መወሰንንና በአገሮቹ መካከል ያለው ድጋፍ ከብድር ይልቅ ወደ እርዳታ አንዲያተኩር ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርም የውይይቱ ትኩረት መሆኑን ያወሱት ዶክተር ዐቢይ ፤ ግንኙነቱን ለማጠናከር በሁለቱም ወገን ከፍተኛ ፍላጎት መንፀባረቁን ገልፀዋል። የኤርትራ ጉብኝታቸውን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ቀደም ሲል ተይዘው የቆዩ አቅጣጫዎችን ትግበራ መመልከት መቻሉን አስታወቀዋል። በተለይም የኤርትራን ወደቦች ሥራ ለማስጀመር የተደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ለመመልከት መቻላቸውን ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መንግስታት መካከል ሁሉን አቀፍ የሶስትዮሽ ውይይት አስመራ ላይ መደረጉንም ጠቅሰዋል። በውይይቱም ጥሩ መግባባትና ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ያብራሩት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያሰ አፈወርቂና የሶማሊያው አቻቸው መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ሁሉን አቀፍ የጋራ የትብብር ሰነድ ፈርመዋል። ስምምነቱ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታን ለማጠናከር እንደዚሁም በአገራቱ መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብትና ልማት ለማፋጠን በጋራ ለመስራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። "በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም በሁሉም መስክ ትብብር መጠናከር ስላለበት ለዚህም ተግተን እየሰራን ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም