የባለድርሻ አካላትን ትብብር በማጠናከር የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው

143

ጋምቤላ ሚያዝያ 19/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የባለድርሻ አካላትን የትብብር ማዕቀፍ በማጠናከር የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋምቤላን ጨምሮ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በፋይናንስ ወንጀሎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።   

የመስሪያ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የባለድርሻ አካላትን የትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ማዕቀፍ በማጠናከር በሀገር ሀብትና ህልውና ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመግታት እየተሰራ ነው።

መስሪያ ቤቱ ከለውጡ በፊት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ የነበረው አደረጃጀት ተልዕኮውን ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለመስሪያ ቤቱ በተሰጠው ትኩረት በበቂ ሁኔታ በመደራጀቱ  የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

መስሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በሀገር ሀብትና ድህንነት ላይ ጉዳት የሚያደረሱ 103 የፋይናስና የሽብርተኝነት ወንጀሎችን በመለየት ለሚመለከታቸው የህግ አካላት እንዲተላለፉ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ለአብነት ጠቅሰዋል።

የፋይናንስና የኢኮኖሚ ወንጀሎች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸሙና ድንበር ዘለል ወንጀሎች ጭምር መሆናቸውን ጠቁመው "መስሪያ ቤቱ ሁሉንም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ባደረገ መልኩ እየሰራ ነው" ብለዋል።

መስሪያ ቤቱ ተደራሽነቱን ለማጠናከርና ተልዕኮውን ለመፈጸም ከየአካባቢው የፍትህ ተቋማትና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

መስሪያ ቤቱ የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራሮችን ለማጠናከር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ጠቁመው በጋምቤላ ክልል የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን አመልክተዋል።

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው "በመስሪያ ቤቱና በክልሉ የፍትህና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተጀመረው የትብብር ማዕቀፍ አሁን ላይ እየተበራከተ ያለውን የፋይናንስ ወንጀል ለመግታት ወሳኝ ነው" ብለዋል።

የትብብርና የቅንጃታዊ አሰራር ማዕቀፉ በተለይም የጋምቤላ ክልል ጠረፋማ ከመሆኑ ጋር ተያያዞ እየተበራከተ ያለውን ህገ-ወጥ የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ፣ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች የፋይናንስ ወንጀሎች ለመግታት የጎላ ፋይዳ ያለው  መሆኑን ተናግረዋል።

በመስሪያ ቤቱ ለክልሉ የፍትህና ሌሎች አካላት የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዘርፉ ለሚከናወኑ ስራዎች አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለጋምቤላ ክልል ዳኞች ፣አቃቢያነ ህግ፣ ፖሊስ፣ የገንዘብና ሌሎች ተቋማት በፋይናንስ ወንጀሎች ዙሪያ ሰሞኑን  በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም