በድርቅና ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ድጋፍ የሚውል አገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ሊካሄድ ነው

110

ሚያዚያ 18/2014/ኢዜአ/ በድርቅና ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ድጋፍ የሚውል አገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ሊካሄድ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

መርሃ-ግብሩን በማስመልከት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን እና ኤልሻዳይ ኢንተርቴይመንት መልቲ ሚዲያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።  

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሀብታሙ ከበደ፤ አገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ እስከ 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት የማሰባሰብ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።    

የአገር ህልውና በማስጠበቅ ሂደት በተለይም ወጣቶች የነበራቸው አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም በድጋፍ ማሰባሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከታህሳስ 1 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም "ወጣትነቴ ለሀገሬ" በሚል መሪ ሐሳብ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ተሰባስቦ ለመልሶ ማቋቋሚያ እንዲውል መደረጉንም አስታውሰዋል።

በደም ልገሳና በስነ-ልቦና ድጋፍ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋቸውንም እንዲሁ።    

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ከወጣቶች ፌዴሬሽን እና ኤልሻዳይ ኢንተርቴይመንትና መልቲ ሚዲያ ጋር በመተባበር የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር መቅረጹን ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጽጌረዳ ዘውዱ፤ በተለይም በወጣቶች አስተባባሪነት የተለያዩ ገቢ ማስገኛ መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።  

ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር በአጭር ጽሑፍ መልእክት ገቢ ማሰባሰብ አንዱ መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሙዚቃ፣ አውደ-ርዕይ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎችም ኩነቶች ይዘጋጃሉ ብለዋል።  

በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ከመደገፍ ባሻገር አንድነትና ህብረትን በማጠናከር በኩል አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም