የ20ኛው ሳምንት ቀሪ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

130

ሚያዚያ 18 /2014 (ኢዜአ) በ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከሚያዚያ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄዱ ሲሆን በዛሬው እለት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በወጣው መርሃ-ግብር መሰረት ከቀኑ 9:00 ሰዓት አርባምንጭ ከተማ ከፋሲል ከነማ ሲጫወቱ ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ተጠባቂው የሀድያ ሆሳዕና እና የሐዋሳ ከተማ ጨዋታ ይካሄዳል።

ሀዋሳ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ከአሥር ወደ ሰባት ነጥብ ዝቅ የሚያደረግ ይሆናል።

ሀድያ ሆሳዕና የሚያደርገው ጨዋታም አሸናፊ ከሆነ ከአሥረኛ ደረጃውን የሚያሻሽል ነው የሚሆነው።

የፋሲል ከነማና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ለተቀመጠው ፋሲል እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ላለው አርባ ምንጭ መሸናነፋቸው የደረጃ ለውጥ ያመጣል።

አዲስ አበባ ከተማ ከአዳማ ከተማ ትናንት ያደረጉት የሊጉ 20ኛ ሳምንት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ወልቂጤ እና ድሬደዋ ደግሞ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ቅዱስ ጊዮርጊስ  በ44 ነጥብ  በአንደኝነት እየመራ ሲሆን፤ ሐዋሳ ከተማ በ34 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ወላይታ ዲቻ ደግሞ ከሐዋሳ ከተማ እኩል 34 ነጥብ ያለው ቢሆንም በጎል ልዩነት ተበልጦ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሰበታ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋርና አዲስ አበባ ከተማ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉ ክለቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም