በክልሉ ተፈናቃይ ወገኖችን ከዕለት ድጋፍ ወደ መልሶ ማቋቋም ለማሸጋገር እየተሰራ ነው

105

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 18 /2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ከዕለት ድጋፍ ወደ መልሶ ማቋቋም ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ተፈናቃይ ወገኖች በበኩላቸው ፤መንግስት በአጭር ጊዜ መልሶ ቢያቋቁማቸው ሰርተው ከተጠባቂነት ለመላቀቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ እንዳሉት፤  በክልሉ ሶስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ተከስቶ በነበረው  ችግር  ከ441 ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በመተከል ዞን እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ ተፈጥሮባቸው በነበሩ አከባቢዎች  በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እና የህክምና መሳሪያዎች፣ የመጠጥ ውሃ እና የአርሶ አደር ማሰልጠኛዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።  

አብዛኞቹ ተፈናቃይ ወገኖች  በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ታረቀኝ፤ የዕለት ደራሽ ምግብን ጨምሮ አቅም በፈቀደ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እየጣለ በሚገኘው ዝናብ ተፈናቃዮቹ ለተላላፊ በሽታዎች እንዳይጋለጡ ጊዜያዊ መጠለያን ለማጠናከር እና መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ማቅረብ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡

የእርዳታ አቀራረቡ ሂደት በተለይም በመተከል ዞን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት እገዛ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአሶሳ እና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ግን የዕለት ደራሽ ድጋፍ በጸጥታ ችግር ምክንያት እየተስተጓጎለ በመሆኑን ድጋፉን በሚገባ ማቅረብ አለመቻሉን አቶ ታረቀኝ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ኮሚሽኑ  ተፈናቃይ ወገኖችን ከዕለት ደራሽ ድጋፍ ባለፈ  በዘላቂነት መልሶ ወደ ማቋቋም ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የሰው ሃይል፣ በጀት እና እስከ አምስት ዓመት እንደሚፈጅ በጥናት ተለይቷል ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በክልሉ መንግስት አቅም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ የፌደራል መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛቸውን  እንዲያጠናከሩ  ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋሙ እቅድ  በአጭር ጊዜ ወደ መሬት እንዲወርድ የክልሉን ሠላም አስተማማኝ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡   

ከተፈናቃዮች መካከል በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ  አቶ ሃብታሙ ዘነበ ኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የ10 ልጆች አባት እንደሆኑና ወደ አካባቢው ከገቡ ስድስት ወራት እንደሞላቸው ተናግረዋል።

የሚሰጣቸው የዕለት ደራሽ ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

ከመፈናቀላቸው በፊት አምርተው  ልጆቻቸው በሚገባ ከማስተማር ባለፈ የተቸገሩትን ሲረዱ እንደነበር አስታውሰው፤ ሰርተው ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከችግር ለማላቀቅ መንግስት በዘላቂነት እንዲያቋቋማቸው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በዘር እና ሌሎች ልዩነቶች መከፋፈሎች ቀርተው ሃገራችን አንድ እንድትሆን እመኛለሁ ብለዋል አቶ ሃብታሙ፡፡

ወይዘሮ እታገኝ ደምስ በበኩላቸው ፤መፈናቀል በተለይ የሴቶችን ህይወት እጅግ ፈታኝ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

መንግስት የጸጥታውን ሁኔታ በዘላቂነት ቢያስተካክል ወደ ቀያቸው ተመልሰው ራሳቸውን መቻል እንደሚፈልጉ ተናግረው፤ ይህም በአካባቢያችው አብረው ያሉት  የአብዛኞቹ ተፈናቃዮች ፍላጎት  እንደሆነ ነው ያመለከቱት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም