የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩኤስኤይድ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር በልማት ትብብር ጉዳዮች ዙርያ ተወያዩ

103

ሚያዝያ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በአሜሪካና ኢትዮጵያ የልማት ትብብር፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ ከዩኤስኤይድ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር ተወያዩ።

ውይይታቸው ያተኮረው በኢትዮጵያ በግጭቶች ምክንያት ስለተከሰቱ ችግሮች፣ በቀጠናው ስለተጋረጠው ረሃብና ወቅታዊው የአለም ሁኔታ ስላስከተለው የምግብ ደህንነት ስጋት ነው።

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ሉዓላዊነት፣ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ መንግስት የሚያከናውነውን የድጋፍና ሰላም የማስከበር እንዲሁም አካታች የፖለቲካ ስርኣት የመገንባት ተግባራት አብራርተዋል።

በተጨማሪም በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ሰብአዊ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ወቅታዊ ትክክለኛ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ያስረዱት አቶ አህመድ ሽዴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከሌሎች አጋር አከላት ጋር እየተከናነወኑ ስለሚገኙ ጉዳዮች ግንዛቤ ሰጥተዋል።

ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) በቀጠናው የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ በውይይቱ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም