የወባ በሽታን ከመላ ሀገሪቱ ለማጥፋት ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ ሊተገብር ይገባል

187

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2014 /ኢዜአ/ የወባ በሽታን ከመላ ሀገሪቱ ለማጥፋት ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ ሊተገብር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ሚያዝያ 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም ወባ ቀን በማስመልከት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም 75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑን ጠቅሰው 52 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖር ተናግረዋል።

በወባ ምክንያት በየዓመቱ የሚከሰተውን የህመምና የሞት መጠን በመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል።

የወባ በሽታን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2030 ከሀገራችን ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስችል  ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ ወደተግባር መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የመከላከል ሥራ የዓለም ጤና ድርጅትን ተቀባይነት ያገኘ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ዶክተር ደረጀ፤ ይህን ውጤት ለማስቀጠል የሁሉም ተቋማትና  ህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወባ በሽታን ከሀገራችን ለማጥፋት በተለይ ህብረተሰቡ የወባ ማስወገድ አፈጻጸም መመሪያዎችንና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ መተግበር አለበት ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ229 ወረዳዎችና በ4ሺህ 400 ቀበሌዎች ላይ ሰፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ከ25 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል፡፡

የአልጋ አጎበር ለሚያስፈልጋቸው ወረዳዎች በ2013 ዓ.ም. ከ8 ሚሊዮን በላይ አጎበር የተሰራጨ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው በተያዘው ዓመትም 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን አጎበር ለማሰራጨት እና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን  ቤቶችን ኬሚካል ለመርጨት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች በጎ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

ወባን ለመከላከል በሀገር ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት በተጨማሪ ከአጎራባች ሀገራት ጋር የተቀናጀ ሥራ እንደሚሰራ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ በተለይ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃና በሀገራችንም ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ወባ ቀን “ፍትሃዊ እና ጠንካራ የጤና ሥርዓት በማጎልበት ወባን እናጥፋ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተጠቁሟል፡፡