ባለፉት 9 ወራት ከ248 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

107

ሚያዝያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት 9 ወራት 248 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው እንዳስታወቁት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 267 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 93 በመቶውን ማሳካት ተችሏል።

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 145 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብሩ ከአገር ውስጥ ገቢ ታክስ ሲሆን ቀሪው ከወጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተገኘ ነው ተብሏል።

ይህም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ 17.1 ከመቶ ዕድገት አለው ብለዋል ሚኒስትሩ።

የገቢ አፈጻጸሙ የተመዘገበው ከዓለም አቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ በተጨማሪ እንደ አገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ነው ያሉት አቶ ላቀ በተለይ 4 የፌደራል ገቢ ሰብሳቢ ቅ/ጽ/ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከሥራ ውጭ በሆኑበትና የተለመደው የንግድ እንቅስቃሴ በተቀዛቀዘበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የገቢዎች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም ገቢያቸውን በወቅቱ አሳውቀው የከፈሉ የፌደራል ግብር ከፋዮችን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም