በአዳማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ1ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ

91

አዳማ  ሚያዝያ 15/2014 /ኢዜአ/ በአዳማ ከተማ የትንሣኤና የኢድ-አል ፈጢር በዓላትን ምክንያት በማድረግ ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ።

የአዳማ ከተማ ደምበላ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ሶሬቻ  ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ ሁሉም ካለው በማካፈል በአላቱን በጋራ ለማሳለፍ ያለመ።

ድጋፉ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መናርን ተከትሎ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ለዓመት በዓል መዋያ እንዳይቸገሩና ተደስተው እንዲያሳልፉ መደረጉን ተናግረዋል ።

ድጋፉ የዳቦ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ዘይት፣ ዶሮ፣ ፍየሎችና በጎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ለአቅመ ደካሞችና የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር ለተሰዉ  የመከላከያ ሠራዊት ቤተሰቦች 70 የመኖሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት መተላለፈፉን ተናግረዋል።

ድጋፉ የአዳማ ከተማ ባለሃብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብና መስተዳድሩ አንድ ላይ በመተባበር የተደረገ መሆኑን አቶ ሶሬቻ ገልፀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ጌቱ ተገኔ "ምንም አይነት የገቢ ምንጭ ሳይኖረኝ ሸራ ወጥሬ ከልጆቼ ጋር ስኖር ነበር" ብለዋል ።

"መስተዳድሩ ዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ መኖሪያ ቤት ሰጥቶናል፣ ፍየልና ዱቄትም አግኝተናል፣ መንግስትና የከተማዋን ነዋሪዎች እናመሰግናለን" ሲሉም አክለዋል።

አቶ ሁሴን ሀቢብ በበኩላቸው "እኔ በግዳጅ ላይ ነበርኩኝ፣ ልጆቼ በግለሰብ ቤት ኪራይ ይኖሩ ነበር፣ መስተዳድሩ የመኖሪያ ቤት ሰጥቶናል፣ አሁን ደስታዬ ወደር የለውም" ብለዋል ።

ሌሎች ለዓመት በዓል መዋያ የሚሆኑ የዘይት፣ ሩዝና ፍየል ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጨምረው ገልጸዋል።

"ሌላው  አስተያየት ሰጪ አቶ ዋበላ ሸሪፍ "አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ ነኝ፤ መንግስት የመኖሪያ ቤት አበርክቶልኛል" ብለዋል።

ሶስት ልጆች ይዘው በግለሰብ ቤት በጥገኝነት የሚኖሩ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ ቤት በማግኘታቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም