በአማራ ክልል 3 ሺህ 141 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተፈቱ

155

ባህር ዳር ሚያዚያ 15/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የትንሳኤና የረመዳን ፆም ፍች በአላትን ምክንያት በማድረግ 3 ሺህ 141 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ገረመው ገብረ ፃዲቅ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ታራሚዎቹ በይቅርታ እንዲፈቱ ወስኗል።

በይቅርታ ከተፈቱት መካከል 3 ሺህ 85ቱ ወንዶችና 56ቱ ሴቶች  መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህግ ታራሚዎቹ የቅርታ የተደረገላቸው የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙና ይቅርታ በሚከለክል ወንጀል ያልተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሙስና ወንጀል ተፈርዶባቸው ከ10 ዓመት በላይ የተወሰነባቸው፣ በመሰረተ ልማት ውድመትና ዘረፋ እንዲሁም በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉና መሰል አደገኛ ወንጀሎችን የፈፀሙ በይቅርታው አለመካተታቸውን አብራርተዋል።

በይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ቀደም ሲል በሰሩት ወንጀል ተፀፅተው ህዝባቸውን በልማት መካስና የወንጀልን አስከፊነት ለህብረተሰቡ ማስተማርና ማንቃት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መስተዳደር ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በይቅርታ ቢፈቱም በመሰል ወንጀል ተሳትፈው የተገኙ የ18 ግለሰቦችን እና በተጭበረበረ መንገድ የይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑ የአምስት ግለሰቦችን ይቅርታ እንዲነሳ መወሰኑን ፍትህ ቢሮ ሀላፊው አቶ ገረመው ገብረ ፃዲቅ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም