የትንሳኤ በዓልን በአቅማችን ልክና በመረዳዳት ልናሳልፍ ተዘጋጅተናል -የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

94

ሆሳዕና:ሚያዝያ 15/2014 (ኢዜአ) የትንሳኤ በዓልን በአቅማችን ልክና የመረዳዳት እሴቶችን በማጠናከር ልናሳልፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ።

በሆሳዕና ከተማ የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ አቶ  ይዲድያ ተስፋሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የአብሮነትንና አንድነትን እሴት ከምናጠናልክርባቸው መካከል የአውደ ዓመት ክብረ በአላት ናቸው።  

"በአውደ ዓመት የተጣሉ ሰዎች ሰላም የሚያወርዱበት፣ የነበረባቸውን ቅሬታ በመፍታት እንደ አዲስ በሰላም ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት የአብሮነት እሴት መገለጫ ነው" ብለዋል።

"በፈጣሪ ፍቃድ ለአውደ አመቱ በሰላም መድረስ በመቻላችን የኑሮ ውድነትና ሌሎች ነገሮችን ችለን  ባለን አቅም ለማክበር ተዘጋጅተናል" ሲሉ አክለዋል።

"ካለን የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍና በመርዳት ማህበራዊ መስተጋብራችንን በማጠናከር በዓሉን ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል" ብለዋል ።

በሆሳዕና ከተማ የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ  ይመኙሻል ፍርዴ በበኩላቸው የትንሳኤ ክርሰቶስ ለሰው ልጅ ሀጢያት ሲል ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት መሆኑን በማሰብ የበደሉትን ብቻ ሳይሆን የበደሏቸውን ጭምር ይቅርታ በማድረግ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል ።

በበአሉ ከጎረቤትና ከዘመድ ጋር የቀደመ የፍቅርና አብሮ የመብላትና የመጠጣት ኢትዮጵያዊ መገለጫን ማጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል ።

"አንዱ ሌላውን  የሚያስብበት ስላለን ብቻ አይደለም" ያሉት ወይዘሮ ይመኙሻል "በአቅማችን ካለን ለሌላው በማካፈል በአብሮነት ተሰባስበን የምናሳልፍበት ወቅት ከፈጣሪ  ዘንድ ታላቅ ገፀ በረከት የምናገኝበት ዕድል ነው" ብለዋል።

ዘንድሮ የተለያዩ ሀገራዊና አካባቢያዊ ችግሮች እንዲሁም የኑሮ ውድነት ቢፈራረቁም በሰላም ለዚህ ጊዜ በመብቃታቸው ባላቸው አቅም ልክ በዓሉን በደስታ ለማክበር መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዘሉ ሚሻሞ ናቸው ።

በአቅም የተዘጋጀን ምግብ በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጎብኘትና በማካፈል ጭምር ለማክበር መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል ።

በፋሲካ የመዳን በአል መሆኑን በመገንዘብ አሁን ከገጠመን ከማንኛውም ችግር መሻገርን እያየን በተስፋ ብርሃን ማከበር እንደሚገባ መክረዋል።

"በበአሉ የፈጣሪ ትዕዛዝ የሆነውን ህብረት እያጠናከርን ከጉድለቶቻችን ይልቅ ምሉዕ በሚያደርጉን የመረዳዳት እሴቶች ላይ ተመርኩዘን ማሳለፍ አለብን" ብለዋል።

"በፈጣሪ እርዳታና ጥበቃ  ለዚህ በዓል መድረስ የቻልንበትን መሰረታዊ ምክንያት  በማስተዋል የሰላምና የአብሮነት  እሴቶቻችንን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባል" ሲሉ አክለዋል ።

የ2014 ዓም የትንሳኤ በዓል በመላው ኢትዮጵያ በነገው ዕለት እንደሚከበት ይታወቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም