ለ300 የጎዳና ተዳዳሪዎች ፆም ማስፈስኪያ መርኃ ግብር ተዘጋጀ

152

አዲስ አበባ ሚያዝያ 15/2014 /ኢዜአ/ የ80ቹ ወርቃማ ትውልድ ዘመን ተጋሪ ጓደኛሞች “እንጀራዬን ለተራቡ ” በሚል ኃሳብ ባዘጋጁት የምገባ መርኃ ግብር በዓሉን ምክንያት በማድረግ 300 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሊያስፈስኩ ነው።

የ“እንጀራዬን ለተረቡ ” መርሃ ግብር በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰባሰቡ የ80ዎቹ ወርቃማ ትውልድ ቡድን አባላት ናቸው።

“የ80ቹ ወርቃማ ትውልድ” ማኅበራዊ ገጽ መሥራች ህሊና ግርማ በመጀመሪያው ዙር በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

በሁለተኛ ዙር ደግሞ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰባሰቡት ገቢ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።  

የሦስተኛው ዙር መርኃ ግብር ለሁለት ወር የቆየ የምገባ መርኃ ግብር መሆኑን ጠቁመው ለ54 ጊዜ  የተለያዩ ድጋፎችን መደረጉን አስረድተዋል።  

በ“እንጀራዬን ለተራቡ ” መርሃ ግብር በቀን እስከ መቶ ሰው የሚደረሱ የጎዳና ተደዳሪ አቅመ ደካማ ሰዎች ሲመግቡ መቆየታቸውንም ነው የገለጹት።

ምገባውን ያከናወኑት የዕለት ጉርሳቸውን ተንቀሳቅሰው ለማግኘት ለተቸገሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች  ቅድሚያ በመስጠት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአዛውንቶች፣ ሕጻናት ለያዙ እናቶችና ለነብሰጡሮች ቅድሚያ መስጠቱን  ተናግረዋል።

የቡድኑ አስተባባሪ እሌኒ ኃይሉ በበኩላቸው የዚህ መርኃ ግብር አካል የሆነው “ፋሲካን ለፍሰካ” 300 የጎዳና ተዳዳሪዎችን በአዲስ አበባ ቦሌ ድልድይ ሥር ያስፈስካል ብለዋል።

በ80ቹ ወርቃማ ትውልድ የፌስቡክ ገጽ ፍቅር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጠናክር ሲሆን ያለፉ አስደሳችና አስተማሪ ትዝታዎችን ለመለዋወጥ አላማም አድርጎ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቡድኑ ለአቅመ ዳካማ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ከላፋት ትውልዶች የወረሱትን እንደ መልካምነትን፣ መረዳዳትን፣ አብሮ መኖርን የመሳሰሉ መልካም እሴቶችን  ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የ80ቹ ወርቃማ ትውልድ የዘመን ተጋሪዎቹ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ አባላት ውልደታቸው ከ1965—1976 ዓ.ም ድርስ የሆነና ልጅነታቸውንና አፍላ ወጣትነታቸውን በ1980ዎቹ ውስጥ ያሳለፉ ናቸው።

ከሁለት ዓመት በፊት የተመሠረተ ይኸው የፌስቡክ ገጽ 163 ሺህ አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም